ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጦርነት፣ በሙስና ክስ እና በተቃውሞ ውስጥ የቆዩት ኔታኒያሁ በምርጫ ያሸንፉ ይሆን?
የእስራኤል የረዥም ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በዚህ ሣምንት በሚደረገው ምርጫ ለሰባተኛ ጊዜ በሥልጣን ለመቆየት ተስፋ አድርገዋል።
ሳቸውን የእስራኤል "የደኅንነት" ዋነኛ አቀንቃኝ አድርገው የሚያርቡት የ77 ዓመቱ ኔታንያሁ ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩት በርካታ እስራኤላውያን በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የደኅንነት ውድቀት አድርገው ከሚመለከቱት ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ጥቃት በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት ከጥቃቱ በኋላ በሐማስ እንዲሁም በአጋሮቹ በሄዝቦላህ እና በኢራን ላይ ጦርነት በማካሄድ ላይ ሲያተኩሩ፤ ኔታኒያሁ የማይቀበሉት የሙስና ክስ በፍርድ ቤት መታየቱ እንደቀጠለ ነው።
የሕዝብ አስተያየት መመዘኛዎች በኔታንያሁ የቀኝ ክንፍ ቡድን እና እሳቸውን ለማስወገድ በጋራ በሚሠሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የጠበቀ ፉክክር እንዳለ ይጠቁማሉ። ከእነዚህም መካከል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት እና የቀድሞው የመከላከያ አዛዥ ጋዲ አይዘንኮት ይገኙበታል።
አሁን ድምጽ በሚሰጡት እስራኤላውያን ዘንድ ሐማስ የፈጸመው ጥቃት ሁነኛ ቦታ እንደሚይዝ ይጠበቃል።
የፖለቲካ ኅልውና
ውዝግቦች እና የፖለቲካ ቀውሶች የሥልጣን ቁጥጥራቸውን አደጋ ላይ ቢጥሉም ኔታኒያሁ በፖለቲካ አፈር ልሰው የመነሳት ዝና አትርፈዋል።
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2022 ለስድስተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በድጋሚ የተመረጡ ሲሆን፤ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም የቀኝ ዘመም የሆነ ጥምረትን ይመራሉ።
ኔታኒያሁ ወደ ሥልጣን የተመለሱት ለ12 ተከታታይ ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበራቸውን ለአጭር ጊዜ በተቃውሞ ካጡ በኋላ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በደጋፊዎች ዘንድ የፖለቲካ አይበገሬው "ንጉሥ ቢቢ" የሚለውን እምነት አጠናክሮታል።
አሁንም ድረስ በበርካታ የቀኝ ክንፍ እና ሃይማኖተኛ መራጮች ዘንድ ተወዳጅ ሆነው ቀጥለዋል። እነዚህ መራጮች በደኅንነት ረገድ ጠንካራ መሪ አድርገው የሚመለከቷቸው እና መንግሥታቸው የሙሉ ጊዜ የሃይማኖት ጥናት ላይ ለሚገኙ አክራሪ ኦርቶዶክስ አይሁዶች ከወታደራዊ ግዳጅ ነፃ እንዲሆኑ ለማድረግ የገፋፋ ነው።
ይሁን እንጂ አሁን የፖለቲካ አይበገሬነታቸው የሐማስ የመስከረም 26 ጥቃት በምርጫው ላይ በጣለው ጥላ ምክንያት በግልፅነት አደጋ ላይ ነው።
ኔታንያሁ እስራኤል በእሳቸው ቁጥጥር ስር እያለች፣ በታሪኳ እጅግ አስከፊ የሆነ ጥቃት ሲፈፀም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ድንበር ሰርገው በመግባት፣ 1,200 የሚያህሉ ሰዎችን ገድለው፤ 251 ሌሎች ታጋቾችን ወደ የወሰዱበት የ2016 ዓ.ም. ጥቃትን ባለማስቆማቸው የተወሰነ ኃላፊነት ወስደዋል።
ነገር ግን እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ጥቃቱ እንዲፈፀም ድክመት ያሳዩ ሌሎች በርካታ ሰዎችም ተጠያቂ እንደሆኑ ይናገራሉ። ባለሥልጣናቱ ከፍተኛ ሠራዊት እንዳያሰማሩ እና ሁኔታውን እንዳያባብሱ በመፍራት ሆነ ብለው እና ቀደም ብለው ከእንቅልፋቸው እንዳልቀሰቀሷቸው በማንሳት ከስሰዋል።
በጋዛ በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጥቃት ቢያንስ 74 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ ቁጥር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተማማኝ ተደርጎ ይወሰዳል። እስራኤል በጋዛ የወሰደችው እርምጃ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰፊ ውግዘት አስከትሏል።
ከጥቃቱ በኋላ ባሉት ዓመታት በራሳቸው የደኅንነት ኃላፊ እንዲሁም የቀጣናው ጎረቤት አገራት ለኔታንያሁ ማስጠንቀቂያዎች እንደተሰጡ የሚገልጹ ዘገባዎች እየጨመሩ መጥተዋል። ይህንንም ኔታኒያሁ አስተባብለዋል።
ባለፈው ወር 'ሃሬትዝ' የተባለው የእስራኤል ጋዜጣ ከአንድ አዲስ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ዘጋባ አውጥቷል። ጽሑፉ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መሪ ሐማስ ለከፍተኛ ዘመቻ ያወጣውን ዕቅድ ለማስጠንቀቅ ከጥቃቱ 10 ቀናት በፊት ኔታንያሁ ደውለው እንደነበር ይጠቅሳል።
የኔታንያሁ ቢሮ ሪፖርቱን "ፍፁም ውሸት" ሲል ውድቅ አድርጎታል፤ ጋዜጣውንም እንደሚከስ ተናግሯል።
በኅዳር 2024 ኔታንያሁ ከሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን፣ ከሱዳኑ ኦማር አልበሽር እና ከሊቢያው ሙአመር ጋዳፊ በመቀጠል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው አራተኛው የአገር መሪ ሆነዋል።
ይህ እና በቀድሞው የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ የወጣው የእስር ማዘዣ በእስራኤል የግራ የቀኝ የፖለቲካ መድረክ ላይ ጠንከር ያለ ቁጣን አስነስቷል።
እነዚህ እርምጃዎች ከመስከረም 26ቱ የሐማስ ጥቃት በኋላ እስራኤል በጋዛ ከወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ጋር የተያያዙ ሲሆን፤ "ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም፣ ሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል፣ ማፈናቀልን እና ሌሎች ኢ-ሰብዓዊ ጥቃቶችን" ተጠቅማለች የሚሉ ክሶችን ያካትታሉ።
ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ክሶቹን ውድቅ ያደርጋሉ።
የወንድም ውርስ
ቤኒያሚን ኔታንያሁ በአውሮፓውያኑ 1949 በቴል አቪቭ ከተማ ተወለዱ። በ1963 ታዋቂ የታሪክ ምሁር እና የጽዮናዊነት ተሟጋች የነበሩት አባታቸው ቤንዚዮን የአካዳሚክ ሥራ አግኝተው ቤተሰባቸው ወደ አሜሪካ ተዛዋወሩ።
በ18 ዓመታቸው ወደ እስራኤል ተመልሰዋል። ከዚያም አምስት ዓመታትን በእስራኤል ጦር አሳልፈዋል። በሠራዊቱ ውስጥ 'ሳዬሬት ማትካል' በተሰኘው ከፍተኛ የኮማንዶ ክፍል ውስጥ ሻምበል ሆነው አገልግለዋል።
በአውሮፓውያኑ 1972 በፍልስጤም ታጣቂዎች በተጠለፈችው የቤልጂየም አውሮፕላን ጥቃት ቆስለዋል። በ1973ቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትም ተሳትፈዋል።
በአውሮፓውያኑ 1976 የኔታንያሁ ወንድም ጆናታን በኡጋንዳ ኢንቴቤ ውስጥ ከተጠለፈ አውሮፕላን ታጋቾችን ለማዳን የተደረገ ዘመቻን ሲመሩ ተገድለዋል። ሞታቸው በኔታንያሁ ቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ስማቸውም በእስራኤል ታዋቂ ነው።
ኔታንያሁ ለወንድማቸው መታሰቢያ የፀረ-ሽብርተኝነት ተቋም ያቋቋሙ ሲሆን፤ በ1982 በዋሽንግተን የእስራኤል ኤምባሲ የምክትል የተልዕኮ ኃላፊ ሆነዋል።
በአንድ ጀንበር የኔታንያሁ ሕዝባዊ ሕይወት ተጀምሯል። ልዩ የሆነው የአሜሪካን አነጋገር ዘይቤ ያላቸው፣ አንደበተ ርቱዕ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ በመሆን በአሜሪካ ቴሌቪዥኖች የተለመዱ ፊት እና የእስራኤል ተሟጋች መሆን ቻሉ።
ወደ ሥልጣን ማማ
ኔታንያሁ በአውሮፓውያኑ 1988 ወደ እስራኤል ሲመለሱ በክነሴት (የእስራኤል ፓርላማ) ውስጥ መቀመጫ አሸንፈው በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ጀምረዋል። የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርም ሆነዋል።
በኋላም የሊኩድ ፓርቲ ሊቀ መንበር እና በ1996 ደግሞ ከይስሃቅ ራቢን ግድያ በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
ኔታንያሁ የእስራኤል በዕድሜ ትንሹ መሪ እና በ1948 እስራኤል ከተመሠረተች በኋላ የተወለዱ የመጀመሪያው መሪ ናቸው።
ኔታንያሁ ምንም እንኳ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የተፈረመውን የ1993ቱን የኦስሎ ስምምነት ቢተቹም፤ በ1997፣ 80 በመቶውን የሚሆነውን የኬብሮን ክፍል ለፍልስጤም አስተዳደር የሚያስረክብ ስምምነት ፈርመዋል።ምንም እንኳን ዕቅዱ እስራኤል ከአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ከመውጣቷ በፊት ቢከሽፍም በሰፈራ ከተያዘው ዌስት ባንክ መውጣትን ተስማምተው ነበረ።
በአውሮፓውያኑ 1999 ከሰባት ወራት በፊት ምርጫ እንዲካሄድ ካደረጉ በኋላ ሥልጣናቸውን አጥተዋል። በቀድሞው የጦር አዛዣቸው እና በሌበር መሪ ኢሁድ ባራክ ተሸንፈዋል።
የፖለቲካ ፉክክር
ኔታንያሁ የሊኩድ መሪነታቸው ሲለቁ በአሪየል ሻሮን ተተክተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2001 ሻሮን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ኔታንያሁ ወደ ሥልጣን ተመልሰዋል፤ መጀመሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዚያም የገንዘብ ሚኒስትር ሆኑ። በ2005 እስራኤል ከያዘችው የጋዛ ሰርጥ መውጣቷን በመቃወም ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል።
በ2005 ሻሮን ከሊኩድ ተገንጥለው 'ካዲማ' የተባለ አዲስ ፓርቲ ሲያቋቁሙ ኔታንያሁ በለስ ቀንቷቸዋል።
ኔታንያሁ የሊኩድ አመራርን በድጋሚ አሸንፈው መጋቢት 2009 ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል።
በዌስት ባንክ የሚካሄድ የሰፈራ ግንባታ እንዲቋረጥ ተስማምተዋል። ይህም ከፍልስጤማውያን ጋር የሰላም ድርድር እንዲኖር አስችሏል። ነገር ግን ድርድሩ በ2010 መጨረሻ ላይ ከሽፏል።
ምንም እንኳን በ2009 በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የፍልስጤም አገርነትን በይፋ መቀበላቸውን ቢገልፁም፤ በኋላ ላይ አቋማቸውን አጠናክረዋል። "ሕዝቡ እንደሚያወራው ሳይሆን የፍልስጤም አገር አይፈጠርም። አይሆንም" ሲሉ በ2019 ለእስራኤል የሬዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሁሉም ሰው "ለአስርት ዓመታት ኅልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥል የፍልስጤም አገር እንዳይመሠረት ያገደ" ሰው ተደርገው እንደሚታወቁ ተናግረው፤ እስራኤል ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምዕራብ በሚገኙ ግዛቶች ሁሉ፣ ጋዛንም ሆነ ዌስት ባንክን ጨምሮ "በምንም ሁኔታ" ሙሉ ለሙሉ የፀጥታ ቁጥጥር እንደምታደርግ አክለዋል።
በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት በተያዘው የዌስት ባንክ የእስራኤል ሰፈራዎች መስፋፋት ጨምሯል። ይህም በተቺዎች ዘንድ የሁለት አገር መፍትሔ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት የሚያወሳስብ ተደርጎ ይታያል።
የአሁኑ መንግሥታቸው በአውሮፓውያኑ 2022 ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ከ100 በላይ አዳዲስ ሰፈራዎችን ፈቅዷል። እንዲሁም ሕገ ወጥ የኮረብታ ላይ መቆጣጠሪያዎችን እና እርሻዎችን በፍጥነት በማስፋፋት ተቆጣጥሯል።
በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ ያሉት ሁሉም የእስራኤል ሰፈራዎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ናቸው።
ኔታንያሁ በፖለቲካ ሕይወታቸው በሙሉ ኢራን ለእስራኤል ትልቁን ስጋት እንደምትፈጥር ደጋግመው አስጠንቅቀዋል። ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመታጠቅ እየሠራች እንደሆነ ሞግተዋል። የዓለም መሪዎች በኢራን መንግሥት ላይ ጠንካራ አቋም እንዲይዙ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ የረዥም ዘመን ዘመቻቸው የካቲት 2026 እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ከፍተው የቴህራንን ከፍተኛ መሪ አሊ ኻሜኔይን ሲገድሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢራን በእስራኤል እና በአሜሪካ ላይ ጥቃት በመሰንዘር አጸፋ ሰጥታለች።
በፓኪስታን አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት በሚያዝያ ወር ተፈርሞ፤ በሰኔ ወር ደግሞ አሜሪካ እና ኢራን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት በጥቂት ሣምንታት ውስጥ ፈርሷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ እና ኢራን ጥቃት ሲሰናዘሩ ቆይተዋል፤ እስካሁንም አዲስ ስምምነት አልተደረገም።
የይስሙላ ክስ
ከአውሮፓውያኑ 2016 በኋላ ኔታንያሁ የሙስና ምርመራ ገጥሟቸዋል። ይህም በ2019 በጉቦ፣ በማጭበርበር እና በሦስት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ እምነት በማጉደል ክስ እንዲመሠረትባቸው አድርጎታል።
የቀረበባቸውን ክስ በመካድ በተቃዋሚዎቹ የተቀነባበረ የፖለቲካ ዓላማ ያለው "የተነጣጠረ ጥቃት" ሰለባ እንደሆኑ ተናግረዋል። ኔታኒያሁ በግንቦት 2020 ችሎት የቀረቡ ሲሆን፤ ይህም ክስ የቀረበባቸው የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጓቸዋል።
ፕሬዝዳንት ይስሐቅ ሄርዞግን ምህረት እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል። ነገር ግን ሄርዞግ የክስ ስምምነት ላይ መድረስ ይቀድማል ብለዋል። ክሱ ከስድስት ዓመታት በላይ መፍትሄ ሳያገኝ ቀጥሏል።
የፍትህ ሥርዓቱን ለማምለጥ የተነሱ አወዛጋቢ ዕቅዶችም ከፍተኛ ተቃውሞዎችን አስነስተዋል። ይህም መስከረም 26 ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት በእስራኤል ብሔራዊ ማንነት እና ዲሞክራሲ ላይ ጥልቅ መከፋፈልን አጋልጧል።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት መሪዋን ለመምረጥ ስትዘጋጅ ያልተፈቱ መከፋፈሎችን ከጀርባዋ ይዛ ነው።
የትራምፕ አጋር
ዶናልድ ትራምፕ በ2017 ፕሬዝዳንት ሆነው መምጣታቸው የአሜሪካ እና የእስራኤል መንግሥት ፖሊሲዎች ይበልጥ እንዲጣጣሙ ምክንያት ሆኗል። ትራምፕ ወደ ሥልጣን በመጡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው መቀበላቸውን አስታውቀዋል።
ይህ እርምጃ ፍልስጤማውያን ከ1967 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወዲህ እስራኤል በያዘችው የኢየሩሳሌም ምሥራቃዊ ክፍል ላይ ያላትን የይገባኛል ጥያቄ በሚደግፉ አረብ ዓለም ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰ ነው። ነገር ግን ለኔታንያሁ ትልቅ የአገር ውስጥ ፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ አሸናፊነት ነው።
ምንም እንኳን በፍልስጤማውያን ዘንድ የአንድ ወገን ተብሎ ውድቅ ቢደረግም፤ በጥር 2020 ኔታንያሁ ትራምፕ በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል የነደፉትን የሰላም ዕቅድ "የክፍለ ዘመኑ ዕድል" በማለት አወድሰውታል።
ኔታኒያሁ እና ትራምፕ በኢራን ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። ፕሬዝዳንቱ በ2018 ከኢራን የኒውክሌር ስምምነት መውጣታቸውን እና የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን እንደገና መጣላቸውን በደስታ ነው የተቀበሉ።
ሆኖም ኔታኒያሁ፣ ጆ ባይደን ሲያሸንፉ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ትራምፕ የእስራኤል መሪ ታማኝ አለመሆንን በመክሰስ አጸያፊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
በሁለቱ መሪዎች መካከል የነበረው ግንኙነት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተስተካክሏል፤ እንደገና ተፈትኗልም።
ትራምፕ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው እስራኤል በኢራን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ደግፈዋል። ኔታንያሁ የሙስና ክሳቸው ይቅርታ እንዲደረግላቸውም ጥረት አድርገዋል። በተደጋጋሚ ወደ ዋይት ሐውስ ጋብዘውም አስተናግደዋቸዋል። ኔታንያሁ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ከጥር 2025 ጀምሮ ስምንት ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ይህም ከማንኛውም የዓለም መሪ በበለጠ ቤተኛ ያደርጋቸዋል።
ትራምፕ ይህን ድጋፋቸውን ከምርጫው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በድጋሚ አጉልተው አሳይተዋል። ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ ኔታንያሁን "ታላቅ ጠቅላይ ሚኒስትር" ብለው በማወደስ "ጠንካራ፣ ደፋር እና ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥማቸው የማይበገሩ ድንቅ መሪ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ከሁሉም በላይ ይህ ምርጫ በአገሪቱ እጅግ ከፋፋይ የፖለቲካ ሰዎች አንዱ በሆኑት ላይ የሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ይታያል። ለደጋፊዎቻቸው ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤልን ደኅንነት ለመጠበቅ አሁንም እንደሚያስፈልጉ ይታመናል። በተቺዎች ዘንድ ደግሞ የፖለቲካ ኅልውናቸው እስራኤልን አደጋ ላይ የሚጥል ተደርጎ ይታያል።