"ገለልተኝነቴን ጠብቄ አገር ግንባታ ላይ ነበርኩ" ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የቆዩ እና የግጭት መንስዔ የሆኑ የተለያዩ አለመግባባቶችን በምክክር የመፍታት ሂደትን እንዲመራ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ጊዜ አገሪቱ በግጭቶች ውስጥ እንዳለች ተጠናቋል።

ታኅሳስ 24/2014 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፣ መጀመሪያ የተሰጠው የሥራ ጊዜ ሦስት ዓመት ነበር። ይሁን እና በተሰጠው ጊዜ ሥራውን ባለማጠናቀቁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11/2017 ዓ.ም ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ ለአንድ ዓመት፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ለስምንት ወራት የሥራ ጊዜው እንዲራዘም ወስኗል።

ኮሚሽኑ በአጠቃላይ በነበረው የአራት ዓመት ከስምንት ወራት ቆይታው ከዝግጅት ጀምሮ አጀንዳዎችን በማሰባሰብ አገራዊ ምክክሩን አካሒዶ ምክረ-ሃሳቦችን እስከመቀበል ያሉ ተግባራትን አከናውኗል።

4,000 ጉባዔያተኞች በተሳተፉበት ምክክር የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ክልሎችን የሚመለከቱትን አጀንዳዎች ለክልሎች ኮሚሽኑ መስከረም 23/2019 ዓ.ም. አስረክቧል።

በብዙ ድጋፎች እና ተቃውሞዎች ታጅቦ ሥራውን ሲያከናውን የቆየው ኮሚሽኑ፣ ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም. የመጨረሻ ቀኑ ሲሆን ኮሚሽነሮቹ እውቅና ተሰጥቷቸው ከወዲሁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሸኝተዋል።

ኮሚሽነሮቹ ከሥራ የተሰናበቱት በአዋጁ ድንጋጌ መሠረት የምክክሩን ምክረ-ሃሳቦች ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ነው።

አጠቃላይ ሂደቱን እና ቀጣይ የምክረ-ሃሳብ ትግበራውን በሚመለከት ለቢቢሲ ማብራሪያ የሰጡት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ የኮሚሽነሮቹ ሥራ ቅዳሜ ጥቅምት 14 በይፋ እንደሚያበቃ ተናግረዋል። የኦዲት ሥራዎችን እና የሂደቱን ውጤቶች በዲጂታል መንገድ የመሠነድ ሥራ የሚያከናውኑ የጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ብቻ ለሦስት ወራት ያህል በሥራቸው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ ከጉባዔው ተሳታፊዎች የቀረቡ እና በኮሚሽኑ የተዘጋጁ 394 ምክረ-ሃሳቦችን ለሚመለከተው አካል ማቅረብን ጨምሮ ምክረ-ሃሳቦቹን ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ ውጭ ያሉ ኃላፊነቶቹን በሙሉ ከሞላ ጎደል ማጠናቀቁን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ምክረ-ሃሳቦችን ለሕዝብ ይፋ ያላደረገው፣ የቀረው ጊዜ ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ባለመሆኑ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

"ምክረ-ሃሳቡን ለሕዝብ የማቅረብ ኃላፊነቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ ስለወሰደ በየደረጃው የሚያቀርባቸው ይሆናል" ብለዋል።

ኮሚሽኑ ምክረ-ሃሳቦቹን አዋጁ በሚሰጠው ሥልጣን ላይ ተመሥርቶ ለሕዝብ ይፋ ቢያደርግ እንኳን፣ ከሕዝቡ ሊነሱ ለሚችሉ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችልበት በቂ ጊዜ የሌለው መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

በመሆኑም ምክረ-ሃሳቦቹ ለሕዝብ ያልቀረቡት፣ "ሙሉ ኃላፊነቱን ለሚወስደው አካል ሰጥቶ ክትትል ባለው መልኩ ለሕዝብ ማቅረቡ ተገቢ ነው በሚል ነው" ሲሉ ምክንያቱን አስረድተዋል።

"ምናልባት ኮሚሽነሮች መንግሥት እንደ አስፈላጊነቱ በፈለገው ቁጥር ልክ በሚያዘጋጀው የክትትል ሞዳሊቲ ውስጥ ገብተው የሚሳተፉ ቢሆን አብረው ሚነሱ ጥያቄዎችን እያስረዱ ይቀጥላሉ። ዛሬ ምክረ-ሃሳቡን አቅርበን በሚቀጥለው ቀን በሌለንበት ሁኔታ ሊመልስ የሚችለው እንግዲህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው" ብለዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት ምክረ-ሃሳቦቹን "በየደረጃው" ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ እንዳረጋገጠላቸው ፕሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል።

የምክረ-ሃሳቦቹን አፈጻጸም በተመለከተ፣ ኮሚሽኑ ለክትትል የሚያስችል ሥርዓት እንደሚዘረጋ በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። ኮሚሽኑ የትግበራው ስትራቴጂ ምን መምሰል እንዳለበት ለምክር ቤቱ ምክረ-ሃሳብ አዘጋጅቶ በማቅረብ በአዋጁ የተጠቀሰውን ኃላፊነት መወጣቱን ዋና ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

ሆኖም ትግበራውን ለመከታተል የነበረው ዕቅድ የኮሚሽነሩ ዕድሜ ባለመራዘሙ እንደማይሳካ ጠቁመዋል።

በቀጣይነት ኮሚሽነሮች ለሦስት ወር ገደማ መብቶቻቸው እየተከበሩላቸው ስለሚቆዩ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ "በቀድሞ ኮሚሽነርነታችን የማማከርም ዕድል ይኖረናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ምንም እንኳን ግዴታቸው ባይሆንም "እኔ ደግሞ እንደዋና ኮሚሽነርነቴ አንዳንድ ሥራዎች መፈፀማቸውን ማየት እፈልጋለሁ" ብለዋል።

በጉባዔው ተሳታፊዎች ከቀረቡ 394 ምክረ-ሃሳቦች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማን ጉዳይ ጨምሮ ጥቂት ምክረ-ሃሳቦች በሰፊ ልዩነት እና አለመግባባት የቀረቡ ናቸው።

በተለይ አዲስ አበባን በሚመለከት የተነሱ ጉዳዮች ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተዋል። ይህም ምክክሩ "ግጭትን ከመፍታት ይልቅ ሌላ የግጭት መንስዔ እንዳይሆን" የሚሉ በርካታ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ምክንያት ሆኖ ነበር።

በተመካካሪዎቹ የቀረቡት "የውሳኔ ምክረ-ሃሳቦች እንጂህ ውሳኔዎች አይደሉም" የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን በበኩላቸው፣ እነዚህ ምክረ-ሃሳቦች ለተግባሪ አካላት በሚቀርቡበት ጊዜ ወዲያው ወደ ተግባር የሚወርዱ ሳይሆኑ "ብዙ ሂደቶችን የሚያልፉ" መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሞያዎች፣ ምክረ-ሃሳቦቹን "በሚገባ ተንትነው የትኛው ነው ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጠቅመው የሚለውን በሚገባ ገምግመው በተቻለ መጠን ከምክረ ሃሳቡ ጋር እንዲመሳሰል ወይም እንዲቀራረብ ካደረጉ በኋላ ነው ወደ ውሳኔ የሚሔዱት" ሲሉም አብራርተዋል።

ከምክክር ሂደቱ ጋር በተገናኘ የኮሚሽኑ አንዳንድ አባላት ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ነበር። በጉባዔው አጀንዳዎች ላይ "እጃቸውን ለማስገባት የሞከሩ" እና ለገዢው ፓርቲ "ወገንተኝነት ሲያሳዩ የነበሩ" ኮሚሽነሮች ስለመኖራቸው የከሰሱ ፓርቲዎች እና የምክክሩ ተሳታፊዎች እንደነበሩ የሚታወስ ነው።

ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ በጉባዔው ሂደት "ኮሚሽነሮች የራሳቸውን ስሜት አንጸባርቀዋል" በሚል የቀረቡ ውንጀላዎችን "እኔ እራሴንም ጨምሮ ያረጋገጥኩበት አካሔድ የለኝም" ሲሉ መልሰዋል።

"እኔም እራሴ በሂደቱ ላይ ተፅእኖ አድርጌ እንደሆነ አላውቅም። ነገር ግን በተቻለ መጠን ገለልተኝነቴን ጠብቄ አገር ግንባታ ላይ ነበርኩ። እስከ መጨረሻው ድረስ ሂደቱን ስከታተል ነበር። ወደዚህም ወደዚያም በሚሄድበት ጊዜ ወደ መሀል የማምጣት ኃላፊነት አለብኝ። ያንን ኃላፊነቴን አቅሜ በፈቀደው መሠረት ተወጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ ሊያቀርብ የሚችልበት የራሱ የሆነ መመሪያ እና ሥርዓት እንዳለው ጠቅሰው ከዚያ ውጭ የሚቀርቡትን ክሶች ግን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል በነበረው እና ወደ ግጭት ካደገው ድባብ ጋር በተገናኘ በምክክር ጉባዔው የሚሳተፉ የክልሉ ተወካዮች በሌሎች ክልሎች በነበረው ሂደት አልፈው የመጡ አለመሆናቸው እንደሚያስቆጫቸው ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ነፍጣቸውን አስቀምጠው ከመንግሥት ጋር እርቅ የፈፀሙ የትጥቅ ታጋዮች በሂደቱ ቢሳተፉም፣ ነገር ግን በትጥቅ ትግል የቀጠሉ ድርጅቶች እና ተወካዮቻቸው አለመሳተፋቸውም ቅር ያሰኛቸው ጉዳይ ነው።

በተጨማሪም፣ አንዳንድ "ተፅእኖ ፈጣሪ" የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደቱ ቢሳተፉ ምኞታቸው እንደነበር እና ብዙ ጥረትም አድርገው እንዳልተሳካላቸው አንስተዋል።

"ነገር ግን" ይላሉ ዋና ኮሚሽነሩ "በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የትኛውም ብሔረሰብ እና የማኅበረሰብ ክፍል ሳይለይ ሁሉም በጋራ ሆነው በአገራቸው ችግሮች ላይ ተወያይተው የውሳኔ ምክረ-ሃሳብ ማቅረባቸው በሌላ መልኩ ይቆጨኛል የምለውን ነገር ያካክሱልኛል።"

በርካታ ኢትዮጵያውያን የአገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ በምክክሩ ተስፋ ያደረጉትን ያህል፣ ምክክሩ አንዳች መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚገልፁም ብዙዎች ናቸው።

ፕሮፌሰር መስፍን በበኩላቸው፣ ምክክሩ ፍሬ እንደሚያፈራ ተስፋ አላቸው። ከኢትዮጵያ ሁሉም ማዕዘናት የተውጣጡ 4,000 ተመካካሪዎች "ተነጋግረን ከነልዩነታችን ምክረ-ሃሳብ በማቅረብ ወደ መግባባት መድረስ መቻላችን በራሱ፣ ምክክር ኢትዮጵያ በሚባል አገር ውስጥ መሥራት እንደሚችል የሚያሳይ ትልቁ የስኬት ጅማሬ ነው" ይላሉ።

ቀጣዩ "ትልቁ ሥራ ትግበራው ነው" የሚሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ የትግበራው መጠን ቀጣዩን ውጤት የሚወስን እንደሆነ ተናግረዋል።

"ግጭት እና ጦርነት ሰልችቶናል። ለቀጣዩ ትውልድ የሚያዋጣው ችግሮችን እና ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በድርድር መፍታት ነው" ሲሉም አክለዋል።

መንግሥት የምክክሩን ምክረ-ሃሳቦች እንደሚተገብር በተደጋጋሚ ገልጿል። በሌላ በኩል ገዢው ፓርቲ በሂደቱ ላይ ጫና እንደፈጠረ እና "ለራሱ በሚፈልገው መንገድ እንደመራው" በመግለፅ ትችት የሚያቀርቡ አካላት፣ ከምክክሩ ምክረ-ሃሳቦች ትግበራ ይልቅ መፍትሔ የሚመጣው ፖለቲካዊ ድርድር በማድረግ እንደሆነ ይሞግታሉ።