ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጀርመን ላይፕዚግ አየር ማረፊያ ውስጥ ለተሞከረው የድሮን ጥቃት ሩሲያ ተጠያቂ መሆኗን ገለጸች
ጀርመን ባለፈው ወር በምሥራቃዊ አገሪቱ ክፍል በሚገኘው የላይፕዚግ አየር ማረፊያ ላይ ለተፈጸመው የድሮን ጥቃት ተጠያቂዋ ሩሲያ መሆኗን በመግለጽ፣ በአገሪቱ የሚገኝ የሞስኮ ቆንስላ ጽሕፈት ቤትን ልትዘጋ ነው።
በሐምሌ መጨረሻ ላይፕዚግ/ሃሌ አየር ማረፊያ ከዩክሬን የጭነት አውሮፕላኖች አጠገብ ፈንጂ የተሸከመ ድሮን ተገኝቶ ነበር።
የፈንጂው ማቀጣጠያ ላይ ብልሽት ስለነበረበት ድሮኑ ሳይፈነዳ ቀርቷል። ሁለተኛው ድሮን ግን በአቅራቢያው ከነበረ የጭነት አውሮፕላን ጋር ተጋጭቷል የሚል ጥርጣሩ በመርማሪዎች ተነስቷል። 10 ቀናት በኋላ ደግሞ አየር ማረፊያው አቅራቢያ ሦስተኛ ድሮን እንደተገኘ ተዘግቧል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንድት፣ የላይፕዚግ አየር ማረፊያ ጥቃት "አውሮፓ ውስጥ የተለመደው የሩሲያ ድብልቅ የዘመቻ አካሄድ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ጀርመን በድጋሚ ዒላማ ልትደረግ ትችላለች የሚል ግምት መኖሩንም ገልጸዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን ጀርመን በላይፕዚግ አየር ማረፊያ ለደረሰው የድሮን ጥቃት ሙከራ ሞስኮን ተጠያቂ ለማድረግ ማስረጃ እየፈበረከች ነው ሲሉ ከስሰዋል። ፑቲን ማክሰኞ ዕለት ላሰሙት ውንጀላ ክስ ማስረጃ አላቀረቡም።
በበርሊን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በበኩሉ ሩሲያ ተጠያቂ ናት መባሉን "ከንቱ" ሲል አጣጥሎታል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዶብሪንድት ግን ጥቅም ላይ የዋሉት መሣሪያዎች ላይ የተደረገው ምርመራ እንዲሁም የስለላ መረጃዎች በጥቃቱ ውስጥ የሩሲያ ተሳትፎ መኖሩን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል።
ይህንን ግኝት ተከትሎ፣ በጀርመኗ ቦን ከተማ የሚገኘው የሩሲያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት እንዲዘጋ እንዲሁም በርሊን ውስጥ ያለው 'ራሽያን ሐውስ' የተሰኘው የባሕል ማዕከል ውል እንዲቋረጥ የሚያደርግ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሃን ዋዴፉል አስታውቀዋል።
ብዙ ታዛቢዎች፣ 'ራሽያን ሐውስ' የተባለው ስፍራ ለስለላ እና ለሩሲያ ፕሮፓጋንዳ ማሠራጫነት ያገለግላል የሚል ክስ ሲያቀርቡ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በጀርመን ድንበሮች በሩሲያውያን ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እንደሚጠብቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሩሲያ በ2022 ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በምዕራባውያን አገራት የተጣሉባትን ማዕቀቦች ለማምለጥ በድብቅ ነዳጅ የምታጓጉዝባቸው መርከቦች ላይ የሚደረገው ጫና እንዲጨምር እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአገሪቱ የሩሲያ አምባሳደር የሆኑትን ሰርጌይ ኔቻዬቭ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጥራታቸውንም አክለዋል። ሚኒስትሩ ይህንን ከተናገሩ ከአጭር ጊዜ በኋላ አምባሳደሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደርሰው ታይተዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ሞስኮ "ተመሳሳዩን በሚያንጸባርቅ" አካሄድ ለጀርመን እርምጃዎች ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
የሩሲያ ኤምባሲ ደግሞ የጀርመንን እርምጃዎች "በሩሲያ እና በጀርመን ግንኙነት ታይቶ የማያውቅ ውጥረት ማባባስ" ሲል ገልጾታል።
የሩሲያዋ ቃል አቀባይ፣ ከጀርመኑ ፕሬስ ኤጀንሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጀርመን ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በመጥቀስ "በርሊን ሽብርተኝነትን እየደገፈች ነው" ብለዋል።
የፀጥታ ባለሙያዎች በአየር መንገዱ ጥቃት ሙከራ የሩሲያ እጅ ሊኖር እንደሚችል ሲገምቱ ቢቆዩም፣ ሞስኮ ግን ተሳትፎ አላት የሚሉ ክሶችን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
በምሥራቃዊ ጀርመን የሚገኘው የላይፕዚግ/ሃሌ አየር ማረፊያ የጀርመን ጦር እና የኔቶ አጋሮች ወታደራዊ ጭነቶችን ለማጓጓዝ የሚጠቀሙበት ነው። ከዩክሬን የአየር ጭነት አብዛኛውን ለሚያጓጉዘው አንቶኖቭ አየር መንገድም ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።