ቀጥታ, ኢልሃን ኦማር በቤቷ ላይ ብርበራ ከተደረገ በኋላ ለቅቃ ለመውጣት መገደዷን ተናገረች

የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነችው ኢልሃን ኦማር ባለፈው ሳምንት የፌዴራል የደህንነት አካላት ቤቷን ከበረበሩ በኋላ ፍተሻው የመኖሪያ አድራሻዋን ለሌሎች አጋልጦ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ውስጥ መኖር እንደማትችል ተናገረች። ኢልሃን ኦማር ቤቷ በፌደራል ጸጥታ አካላት ከተበረበረ በኋላ በሰጠችው የመጀመርያ ቃለ ምልልስ “እየደረሱብኝ ያሉት የግድያ ዛቻዎች እንዳሉ ሆነው፣ እኔና ልጆቼ በዚያ ቤት ውስጥ መኖራችን ከአሁን በኋላ አስተማማኝ አይደለም” ብላለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢልሃን ኦማር በቤቷ ላይ ብርበራ ከተደረገ በኋላ ለቅቃ ለመውጣት መገደዷን ተናገረች

    ኢልሃን ኦማር

    የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነችው ኢልሃን ኦማር ባለፈው ሳምንት የፌዴራል የደህንነት አካላት ቤቷን ከበረበሩ በኋላ ፍተሻው የመኖሪያ አድራሻዋን ለሌሎች አጋልጦ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ውስጥ መኖር እንደማትችል ተናገረች።

    ኢልሃን ኦማር ቤቷ በፌደራል ጸጥታ አካላት ከተበረበረ በኋላ በሰጠችው የመጀመርያ ቃለ ምልልስ “እየደረሱብኝ ያሉት የግድያ ዛቻዎች እንዳሉ ሆነው፣ እኔና ልጆቼ በዚያ ቤት ውስጥ መኖራችን ከአሁን በኋላ አስተማማኝ አይደለም” ብላለች።

    ኦማር ኤምኤስኤን ናው ለተባለ መገናኛ ብዙኃን የአገር ውስጥ ደህንነት ሠራተኞች ስልኮቿን ጨምሮ ማስታወሻ ደብተሮቿን እና በርካታ ንብረቶቿን ለምርመራ በሚል መውሰዳቸውን ተናግራለች።

    መንግሥት ኦማር በምን ወንጀል እንደተጠረጠረች ባይናገርም ነገር ግን ብርበራው የተካሄደው “ከፌደራል ወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ” መሆኑን ገልጿል።

    ኦማር ቤቷ ከመመርመሩ በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ካገኘችው የአሜሪካ ዜግነቷን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎ ቀርበውባት ነበር።

    በምርመራው ሂደት ውስጥ፣ የኦማር ቤተሰብ አባላት ላይ ከአስራ ሁለት በላይ የፍርድ ቤት መጥሪያዎች ወጥተዋል። እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ፣ የግል ኮምፒውተሮቿ እና ፓስፖርቷ ከተያዙት ንብረቶች መካከል ይገኙበታል።

    በቤቷ ላይ ለሰዓታት ለቆየው ፍተሻ በተመለከተ ለኤምኤስ ናው አስተያየቷን የሰጠችው ኦማር፣ “ይህ በእርግጠኝነት ሁላችንንም በጣም አስደንግጦናል” ብላለች።

    ኦማር የደህንነት አባላት እርሷ እና ባለቤቷ እንቅልፍ ላይ እያሉ “በራችንን ደብድበዋል” ስትል ፍተሻው የተደረገበትን ሁኔታ አብራርታለች።

    “እየጮህን ነበር” ያለችው ኦማር፣ ጥንዶቹ ከመኝታ ክፍላቸው ወደ በሩ እየሮጡ መጥተው መክፈታቸውን ሁኔታው “እጅግ እንግዳ ነገር” እንደነበርም አስረድታለች።

    ኦማር ከ15 እስከ 25 የሚሆኑ የደህንነት አባላት ቤቷን መክበባቸውን ነገር ግን ሁሉም “በሥነ ስርዓት ሥራቸውን ማከናወናቸውን” ገልጻለች።

    የደህንነት አባላት በር ላይ እያሉ የፍርድ ቤት ማዘዣ ይዘው እንደሆነ መጠየቋን እና ማሳየታቸውን ጨምራ አብራርታለች።

    የደህንነት አባላቱ ብርበራውን ሲያከናውኑ ሶፋ ላይ ተቀምጣ መመልከቷን የገለፀችው ኢልሃን ኦማር አምስት ያህል የፈጀ ብርበራ መካሄዱን ጨምራ አስታውቃለች፥።

    የእጅ ስልኮች፣ ማስታወሻ ደብተሮች እና የባለቤቷን ካሜራ ጨምሮ 17 ነገሮች መውሰዳቸውንም ተናግራለች።

    ቢቢሲ የአሜሪካ ፍትህ ቢሮን ለማነጋገር ቢጠይቅም ወደ አገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ተመርቷል።

    መንግሥት ምርመራውን ያደረገበትን መንገድ የተቸችው ኦማር ለማስፈራራት ታስቦ የተደረገ እንደሆነ ገልጻለች።

    ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ብርበራ ዙሪያ፣ ኦማር በኢንተርኔት ላይ በለቀቀችው መግለጫ ድርጊቱን “ከባድ የሥልጣንን አላግባብ መጠቀም” ያለች ሲሆን ባለስልጣናት የፌዴራል ሕግ አስከባሪ አካላትን በመጠቀም የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ዒላማ እያደረጉ ነው ስትል ከስሳለች።

    የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ብርበራውን አጥብቀው የተቹ ሲሆን፣ ድርጊቱንም “እጅግ አስቀያሚ” ሲሉ ገልጸውታል።

  2. ከአንድ ዓመት በላይ በኒጀር ታግተው የነበሩት ሁለት አውሮፓውያን ሊቢያ ውስጥ ተለቀቁ

    የ76 ዓመቷ ኢቫ ግሬትዝማቸር በኒጀር ለብዙ ዓመታት በእርዳታ ድርጅት ውስጥ ሰርታለች
    የምስሉ መግለጫ, የ76 ዓመቷ ኢቫ ግሬትዝማቸር በኒጀር ለብዙ ዓመታት በእርዳታ ድርጅት ውስጥ ሰርታለች

    አንድ የስዊዝ እና አንዲት ኦስትሪያዊ ከአንድ ዓመት በፊት በኒጀር ከታገቱ በኋላ በሊቢያ ቤንጋዚ መለቀቃቸውን ተገለጸ።

    የ76 ዓመቷ ኦስትሪያዊት ኤቫ ግሬትዝማቸር እና የ69 ዓመቷ ስዊዘርላንዳዊት ክላውዲያ አብት፣ ባለፈው ዓመት ጥር እና ሚያዚያ ወራት በሰሜናዊ ኒጀር አጋዴዝ ከተማ ታግተው ተወስደው ነበር።

    ግለሰቦቹን ያገታቸው ማን አንደሆነ እና ፍላጎታቸው ምን እንደነበር አልተገለጸም።

    ሁለቱ አውሮፓውያን በምን ስምምነት እንደተለቀቁም የተባለ ነገር የለም።

    የኦስትሪያ እና የስዊዘርላንድ መንግሥታት ግለሰቦቹ መለቀቃቸውን አረጋግጠዋል።

    የስዊዘርላንድ መንግሥት አብት ነጻ እንደወጣችና ወደ አገሯ በመመለስ ላይ እንደምትገኝ የገለጸ ሲሆን፣ የኦስትሪያ መንግሥት በበኩሉ ግሬትዝማቸር "ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች" ከተደረጉ በኋላ መለቀቋን አስታውቋል

    "ኤቫ ከ21 ወራት በላይ በእገታ ስር ከቆየች በኋላ ነጻ በመውጣቷ ሁላችንም ከፍተኛ እፎይታ ተሰምቶናል፣ ለበርካታ ወራት ከቀጣናዊ፣ ከአውሮፓውያን እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር በቅርበት፣ በስውር እና በመተማመን መንፈስ ስንሰራ ቆይተናል። እነዚህ የጋራ ጥረቶችም ፍሬ አፍርተዋል" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤአቴ ሜይንል ራይዚንገር በመግለጫቸው ተናግረዋል።

    የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በቤንጋዚ ከአብት ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን የሕክምና ድጋፍ ተሰጥቷታል ብሏል።

    "ካሳለፈችው ሁኔታ አንጻር በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፤ በአሁኑ ወቅትም ወደ ስዊዘርላንድ በመመለስ ላይ ትገኛለች" ሲልም ገልጿል።

    ግሬትዝማቸር ለብዙ ዓመታት በኒጀር የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ የነበረች ሲሆን፣ አብት ደግሞ በአጋዴዝ ለበርካታ ዓመታት የማኅበረሰብ ሠራተኛ በመሆን አገልግላለች።

  3. ኢራን ሰባት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማለፍ ሲሞክሩ መመታታቸውን አስታወቀች

    መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ

    ኢራን ሌሊቱን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ሰባት መርከቦች በተተኳሽ ወይንም በፈንጂ ተመትተው በእሳት መያያዛቸውን አስታወቀች።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባህር ኃይል ሐሙስ ዕለት በሰሜናዊው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር ላይ የተሳተፉ አራት መርከቦች ክትትል ከተደረገባቸው በኋላ ተመትተው በእሳት ተያይዘዋል ብሏል።

    አክሎም ሦስት ተጨማሪ መርከቦች ከሆርሙዝ ወሽመጥ በስተ ምዕራብ በፈንጂ ተመትተው በእሳት ተያይዘዋል ብሏል።

    አብዮታዊ ዘቡ በቀጣይ ትንኮሳ የሚኖር ከሆነ በቀጣናው በሚገኙ የጦር ሠፈሮች ላይ መጠነ ሠፊ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

    ይህ የቴህራን እርምጃ በቀጣናው ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ባየለበት ወቅት የተፈጸመ ነው።

    በእስራኤል የሚካሄደው እንዲሁም በአሜሪካ የሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ጥቂት ሳምንታት በቀሩት በዚህ ወቅት የኢራን ጥቃት የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ይፈጥራል ተብሎ ተፈርቷል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ዳግም ይጀምራሉ የሚል ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈጥሯል።

    “ኔታንያሁ ኢራንን ማጥቃት ይፈልጋሉ፤ ይህ አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም” ሲሉ በእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑትና ቀደም ሲል በእስራኤል ወታደራዊ እና የስለላ ተቋማት ውስጥ የኢራን ጉዳይ ባለሙያ በመሆን ያገለገሉት ዳኒ ሲትሪኖዊች ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

    እስራኤል ስትራቴጂዋን ሳታሻሽል ከኢራን ጋር ወደ ሌላ ግጭት ለመግባት እየተጣደፈች ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    ከአምስት ቀን በኋላ ጥቅምት 27 በሚካሄደው ምርጫ ኔታንያሁ በግልጽ ካሸነፉ፣ ጥቃት የመሰንዘሩ ዕድል እጅግ ከፍተኛ ወይም እርግጠኛ ማለት ይቻላል ሲሉም አስተያየታቸውን አጠናቅቀዋል።

  4. በምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ

    ዳማም በሳዑዲ አረቢያ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኝ ትልቋ ከተማ ናት
    የምስሉ መግለጫ, ዳማም በሳዑዲ አረቢያ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኝ ትልቋ ከተማ ናት

    በረቡዕ ምሽት በምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያ ዳማም ከተማ በአውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ስምንት መቁሰላቸውን የአገሪቱ የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    በንጉሥ ፋሃድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተገደሉት የሳዑዲ እና ሕንዳዊ ዜጎች መሆናቸውን ባለሥልጣናቱ ገልጸው የተጉዱት ደግሞ የሳዑዲ፣ የመን፣ ሕንድ፣ ባንግላዲሽ እና የኔፓል ዜጎች ናቸው ተብሏል።

    የሲቪል አቪየሸን ባለሥልጣናቱ ስለ ደረሰው ጥቃት ዓይነት ማብራሪያ ያልሰጡ ቢሆንም የየመን ሁቲዎች ግን በተደጋጋሚ የሳዑዲን አውሮፕላን ማረፊያዎች በድሮኖች እና ሚሳዔሎች ሲያጠቁ ነበር።

    ረቡዕ ማለዳ ወደ አገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ተተኩሶ የነበረ ድሮን እንዲከሽፍ ከተደረገ በኋላ በወደቁ ስብርባሪዎች ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

    የሳዑዲ አረቢያ ኤነርጂ ሚኒስቴር ድሮኖቹ ዒላማ ያደረጉት የአገሪቱን የነዳጅ ማቀነባበሪያን እንደነበር ገልጾ አንድ መኪና በእሳት መቃጠሉን አስታውቋል።

    ሁለቱ በድሮን ስብርባሪዎች የሞቱት ሰዎች የፊሊፒንስ እና ኔፓል ዜጋ መሆናቸው ሲገለጽ፣ ረቡዕ ምሽት ተጨማሪ አራት ወደ አካባቢው የተተኮሱ ድሮኖች እንዲከሽፉ መደረጉ ይፋ ሆኗል።

    ሁቲዎች ስለጥቃቱ ወዲያውኑ ምላሽ ባይሰጡም ከዚህ በፊት ግን የሳዑዲን አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኢነርጂ ተቋማት እና ወታደራዊ ጦር ሠፈር እንደሚያጠቁ ተናግረዋል።

  5. ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የሰላም ድርድር ለመቀጠል ከተስማማች በኋላ ኪየቭ በሚሳዔሎች ተመታች

    በዩክሬን ኪየቭ በሩሲያ ጥቃት በተጎዱ መኪኖች እና በአፓርታማ ፍርስራሽ ፊት ቆማ ስልክ እያወራች ያለች አንዲት ሴት የምትታይበት ፎቶ
    የምስሉ መግለጫ, በቅርብ ሳምንታት ሩሲያ በኪየቭ እና በሌሎች የዩክሬን ከተሞች ላይ የምትፈፅማቸውን ገዳይ የሚሳዔልና የድሮን ጥቃቶች አጠናክራለች

    ሩሲያ የሰላም ድርድሩን ለመቀጠል "በመርህ ደረጃ ዝግጁ" መሆኗን ከገለፀች እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዓለም ጦርነቱን ወደ ማስቆም "ከእስካሁኑ ይልቅ የቀረበችበት" ደረጃ ላይ መሆኗን ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ፣ የዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ የሚሳዔል ጥቃት ተፈፀመባት።

    የኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ እንዳሉት፣ ድርድሩን ለመቀጠል ሩሲያ ከአሜሪካ ለቀረበው ሃሳብ ስምምነቷን ከገለፀች በኋላ ረቡዕ ምሽት በፈፀመችው ጥቃት በርካታ ቤቶች የተመቱ ሲሆን ስድስት ሰዎች ቆስለዋል።

    ጥቃቱ የዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኞች ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር የሚመሩት አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በተጠናከረበት ወቅት ነው የተፈፀመው።

    ዊትኮፍ ከዩክሬኑ መሪ ጋር ከተገናኙ ከአንድ ቀን በኋላ ረቡዕ ዕለት በሴንት ፒተርስበርግ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተዋል።

    የሦስትዮሽ ድርድሩ ከየካቲት ወር ጀምሮ እንደተቋረጠ ቀጥሎ ነበር። ድርድሩ ከተቋረጠ በኋላ ባሉት ጊዜያት ዩክሬን ከምዕራባውያን አገራት የተሰጣት የሚሳዔል መቃወሚያ መሣሪያዎች እያለቁባት በመምጣታቸው፣ ሩሲያ ጥቃቶቿን አጠናክራ ቀጥላለች።

    ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ሲናገሩ "ከጥቂት ቀናት በፊት ከቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን ላይ እያደረገ ያለውን ጦርነት ስለማስቆም ተነጋግሬ ነበር። በዚህም ረገድ [ለማስቆም] እየተቃረብን ያለን ይመስለኛል፤ ምናልባትም አሁን ላይ እስካሁን ከደረስንበት ሁሉ በጣም የቀረብንበት ደረጃ ላይ ነን" ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጦርነቱን ማስቆም እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ እስካሁን የሩሲያና የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም አልቻሉም።

    የፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ ዊትኮፍ፣ በሴንት ኢተርስበርግ ፑቲንን ከማነጋገራቸው አስቀድመው ማክሰኞ ዕለት ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌኒስኪ በተጨማሪ የኖርዌይ እና የፊንላንድ መሪዎችንም በኖርዌይ ዋና ከተማ አግኝተው አነጋግረዋል።

    ዊትኮፍ ለፑቲን ስላቀረቡት ዝርዝር ሃሳብ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ዜሌኒስኪ በበኩላቸው ከልዩ መልዕክተኛው ጋር ካደረጉት ንግግር በኋላ ለዩክሬን ስለሚሰጥ ጠንካራ የደኅንነት ዋስትና እና የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም በቀረበላቸው ሃሳብ ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል።

    ጦርነቱን ማቆም በሚቻልበት መንገድ ላይ የአሜሪካ፣ የሩሲያ እና የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በርካታ ዙር ውይይቶችን አድርገዋል።

  6. ዩናይትድ ኪንግደም በአርክቲክ ቀጣና ለሩሲያ ጥቃት መጋለጧ ተገለጸ

    የዩኬ ወታደራዊ መርከብ

    ዩናይትድ ኪንግደም በአርክቲክ ቀጣና የመከላከል አቅሟ ላይ “ክፍተት” እንዳለ እና ይህም ለሩሲያ ጥቃት እንደሚያጋልጣት የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች አስጠነቀቁ።

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመከላከያ ኮሚቴ እንዳለው፤ የዩኬ ወታደራዊ መርከቦች እና ሰርጓጅ መርከቦች ውስንነት አገሪቱን ተጋላጭ አድርጓል።

    በአርክቲክ ቀጣና ያሉ ከባሕር በታች የተቀበሩ ኬብሎች እና የኢነርጂ አቅርቦትም ተጋላጭ መሆናቸው ተገልጿል።

    ግጭት ቢነሳ ሩሲያ ለዩኬ ሕዝብ እንዲሁም ለሲቪሎች እና ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች ስጋት እንደምትጋርጥ ተመልክቷል።

    የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር ሩሲያ ስጋት መሆኗን “በግልጽ እንደሚገነዘብ” አስታውቋል። የአገሪቱን ከባሕር በታች ያሉ ኬብሎች ለመጠበቅ ከፍተኛ ገንዘብ ማፍሰሱንም አክሏል።

    የአርክቲክ ክበብን የያዘው ሀይ ኖርዝ ቀጣና በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቁልፍ የዩኬ መከላከያ ስጋት ሆኗል።

    በአውሮፓውያኑ 2026 መባቻ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው፤ በሰሜne አትላንቲክ ያለው የሩሲያ የሰርጓጅ መርከብ እንቅስቃሴ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋር የሚመሳሰል ነው።

  7. የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት የውጭ አገራት መሪዎች በአገሪቱ የተፈጠረውን አመፅ ተጠቅመውበታል በማለት ከሰሱ

    አስለቃሽ ጭስ በሞላው መንገድ መሃል የፈረንሳይ ባንዲራ ለብሶ የቆመ ሰው

    የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የውጭ አገራት መሪዎች ቅዳሜ ዕለት በመላው አገሪቱ የተቀሰቀሰውን አመፅ ለራሳቸውን የምርጫ ዓላማ እየተጠቀሙበት ነው በማለት ከሰሱ።

    ማክሮን ይህንን አድርገዋል ያሏቸውን መሪዎች በስም ባይጠቅሱም፣ የኑሮ ውድነትን በመቃወም ተጀምሮ ወደ አመፅነት የተቀየረውን ክስተት በተመለከተ በሚሰጧቸው አስተያየቶች አማካኝነት፣ “በፈረንሳይ ኪሳራ” ለመጪው ምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ይህንን ያሉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት፣ መሪዎቹን “በዚህ ቀጣናምን ይሁን በሌላኛው የአትላንቲክ አቅጣጫ የምርጫ ቅስቀሳ ድባብ ውስጥ ያሉ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

    ይህ አገላለጽ በሚቀጥለው ሳምንት ፓርላሜንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እንዲሁም በሚቀጥለው ወር አጋማሽ የሥልጣን ዘመን ምርጫ ለሚካሄድባትን አሜሪካ የሚመሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያነጣጠረ ይመስላል።

    እንደ ማክሮን ገለጻ፣ ስማቸውን ያለተጠቀሱት መሪዎች አመፁን በተመለከተ በተሰራጩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቪዲዮዎች ተጽፅኖ ደርሶባቸዋል።

    ፓሪስ፣ ሊዮን እና ማርሴይን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን ያመሰው አመፅ ከተነሳ ወዲህ 150 ገደማ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን ከ800 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

    ጭንብል ባጠለቁ ተቃዋሚዎች እና ፖሊሶች መከካል ግጭት ሲፈጠር እንዲሁም ንብረቶች ሲወድሙ ሱቆች ሲዘረፉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተሰራጭተዋል።

    መንግሥት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሁኔታ ላይ ተማሪዎች ለሳምንታት ያካሄዷቸውን ተቃውሞዎች ተከትሎ በተቀሰቀሰው አመፅ ወቅት የፖሊስ ኃይሉ “ቁጥጥር አጥቶ” እንደነበር የአገሪቱ መንግሥት አምኗል።

    ፕሬዝዳንት ማክሮን ለአመፁ ተጠያቂ ያደረጉት “ከፅንፈኛ ግራ ዘመም ቡድኖች የወጡ አቀጣጣዮችን” ሲሆን ባለሥልጣናት “የማያወላውል” እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

    ማክሮን በኳታር ዶሃ ከተማ ባደረጉት ንግግር “እንደ እኔ፣ በተፈጠሩት ክስተቶች ውስጥ የሚታይ የውጭ ጣልቃ ገብነት የለም። በሌላ በኩል ግን ከዚያ በኋላ የመረጃ ማዛባት ነበር፤ ይህም ከውጭ መሪዎች እና ከበርካታ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው እና የሞኝነት አስተያየቶች እንዲሰጡ በር ከፍቷል” ብለዋል።

  8. ፌስቡክ ተጠቃሚዎቹን ‘በመዋሸቱ’ ሜታ 25 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ታዘዘ

    ማርክ ዙከርበርግ

    ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕን የሚያስተዳድረው ሜታ 25 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል በፍርድ ቤት ታዘዘ።

    የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ የያዘበትን ሁኔታ በተመለከተ ለዓመታት ለሕዝቡ የሰጠው መረጃ ሐሰተኛ ነው በሚል በኒው ሜክሲኮ ፍርድ ቤት ፍርድ ተሰጥቷል።

    ሜታ ከዚህ ቀደም ከተጣሉበት ቅጣቶች ባጠቃላይ የአሁኑ ከፍተኛው ነው።

    ለሁለት ሳምንት የቆየው የፍርድ ሒደት ሲጠናቀቅ ዳኛው “ውሸቱ የፌስቡክ መረጃ አያያዝን ብቻ የተመለከተ አይደለም፤ መሠረታዊ የፌስቡክ የንግድ አካሄድንም ይመለከታል” ብለዋል።

    የሜታ ዋና ጠበቃ ሲጄ ማሆኒ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “በኒው ሜክሲኮ መሥራት እንዳንችል ያደርጋል” ብለዋል። ሜታ አቤቱታውን ለፍርድ ቤት እንደሚያቀርብም ተናግረዋል።

    ሜታ ከዚህ ቀደም በቀረቡበት የተለያዩ ክሶች የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል። በቅርቡ ከተላለፉ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች መካከል ከልጆች ደኅንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ በካሊፎርኒያ ተከስሶ 18 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል መደረጉ ይጠቀሳል።

    ‘የኬምብሪጅ አናሊቲካ ቅሌት’ በሚል የሚታወቀው ክስተት፤ ፌስቡክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎቹን መረጃ አሳልፎ በመስጠት ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር መዋሉን ያሳየ ነው።

    ይህም በአውሮፓውያኑ 2016 ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲመረጡ ከተደረገው ንቅናቄ ጋርም ይገናኛል።

    በኒው ሜክሲኮ ፍርድ ቤት የቀረበው ሜታ የተጠቃሚዎችን መረጃ የሚገለገልበትን መንገድ በተመለከተ ሆነ ብሎ ሕዝብን አሳስቷል ተብሏል።

  9. የሁቲዎች ጥቃት መባባሱን ተከትሎ አሜሪካ የተወሰኑ ዲፕሎማቶቿ ከሳዑዲ አረቢያ እንዲወጡ አዘዘች

    ሁቲዎች ጥቅምት መጀመሪያ ላይ በሪያድ የሚገኝ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል
    የምስሉ መግለጫ, ሁቲዎች ጥቅምት መጀመሪያ ላይ በሪያድ የሚገኝ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል

    ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን እና በመላው አገሪቱ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተወሰኑ ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸው ሳዑዲን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘ።

    በነዳጅ ማውጫ ሥፍራ ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከረ ድሮን በተጠለፈበት ወቅት ስብርባሪዎች ሁለት ሰዎችን መግደላቸውን የሳዑዲ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ዳማም ከተማ ውስጥ በሚገኘው የኪንግ ፋህድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ደግሞ አንድ ሰው እንደተገደለ ተገልጿል።

    በኢራን በሚደገፉት የየመን ሁቲዎች እና ሳዑዲ አረቢያ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ካለፈው ወር አንስቶ እየተባባሰ ነው።

    በሳዑዲ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ምላሽ የሰጡት ሁቲዎች በአገሪቱ አየር ማረፊያዎች፣ የኢነርጂ ተቋማት እንዲሁም ጦር ሠፈሮች ላይ ሚሳዔል እና ድሮን አስወንጭፈዋል።

    በሪያድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የደረሰው ጥቃት ሳዑዲ በዓመታት ጊዜ ውስጥ ካስተናገደቻቸው ጥቃቶች ውስጥ ከፍተኛ የሞት ቁጥር የተመዘገበበት ሆኗል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ፣ “የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ያልሆኑ የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች እና የቤተሰብ አባላቶቸቻው ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል” ብለዋል።

    “በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በሲቪል አየር ማረፊያዎች እና በሌሎች ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ጨምሮ ሳዑዲ አረቢያ ላይ የሚፈጽሙት ጠብ አጫሪ ድርጊቶች ጨምረዋል” በማለትም ገልጿል።

    እነዚህ ጥቃቶች በንጹኃን ላይ ሞት ማስከተላቸውን እና ከባድ የጉዞ መስተጓጎል መፍጠራቸውንም ተቅሷል።

    በተጨማሪም ቃል አቀባዩ “የጥቃት ድርጊቶቹ በፍጥነት ሊባባሱ የሚችሉበት ዕድል አለ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  10. አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ወታደሮቿን እየቀነሰች መሆኑ ተዘገበ

    የአሜሪካ ወታደሮች

    የሁቲዎች ጥቃት እና ኢራን የደቀነችው ስጋት በመባባሱ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ወታደሮቿን እየቀነሰች መሆኑ ተዘገበ።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ አንድ የአገሪቱ ባለሥልጣን እና አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የዋሽንግተን ወታደሮች ቀስ በቀስ እንዲወጡ እየተደረገ ነው።

    አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ የጦር ሰፈሮቿ ወታደሮችን እየቀነሰች ያለችው “እምብዛም ስለ ጉዳዩ ሳይሰማ” መሆኑን የሲቢኤስ ምንጮች ትናንት ረቡዕ ገልጸዋል።

    ዘገባውን ከሌሎች የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ቀድሞ ያወጣው ሲቢኤስ ነው።

    ዘገባውን ተከትሎ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ካፕቴን ቲም ሀውኪንስ ለሲቢኤስ በሰጡት ምላሽ “በየጊዜው ወታደራዊ ኃይላችንን እና መሣሪያችንን እናንቀሳቅሳለን” ብለዋል።

    እንቅስቃሴው የሚደረገው “ወታደራዊ ዝግጁነትን ለማሳደግ” መሆኑን ገልጸዋል።

    ሆኖም ግን የወታደራዊ ተልዕኮዎች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን ከእንቅስቃሴዎቹ ጋር የተያያዘ መረጃ እንደማይሰጥ ተናግረዋል።

    “የአሜሪካ ጦር በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ ፍላጎቶችን ለማስጠበቅ ዝግጁ ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።

  11. ጋምቢያ ከቀድሞ መሪዋ ያህያ ጃሜህ ከተወረሰ የአሜሪካ መኖሪያ ቤት ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ ተጎጂዎችን ልትክስ ነው

    የቀድሞው የጋምቢያ መሪ ያህያ ጃሜህ
    የምስሉ መግለጫ, በአሁኑ ወቅት በኢኳቶሪያል ጊኒ በስደት የሚኖሩት የቀድሞው የጋምቢያ መሪ ጃሜህ አገሪቱን ከ20 ዓመት በላይ መርተዋል

    ለረዥም ጊዜ ጋምቢያን ከመሩት ያህያ ጃሜህ ንብረት ውርስ ሽያጭ በተገኘ እና ከአሜሪካ በተላለፈ ገንዘብ፣ በአገዛዛቸው ወቅት ለተጎዱ ሰዎች ካሳ እንደሚከፈል የአገሪቱ ባለሥልጣናት ገለፁ።

    የጋምቢያ የካሳ ኮሚሽን፣ የቀድሞው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር መሪ በነበሩት ጃሜህ ስም የነበረ በሜሪላንድ ከሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ሽያጭ የተገኘ 2.5 ሚሊዮን ዶላር መቀበሉን ገልጿል።

    አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2022፣ ንብረቱ "በወንጀል በተገኘ እና ያለአግባብ በተወሰደ የጋምቢያ የሕዝብ ገንዘብ" የተገዛ ነው በሚል እንዲሸጥ ወስናለች።

    ጃሜህ እአአ በ1994 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙ በኋላ ጋምቢያን ከ20 ዓመታት በላይ መርተዋል። የአገዛዛቸው ዘመን በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሰዎችን በግዳጅ በመሰወር እና ከፍርድ ውጭ ግድያዎችን መፈፀም ክሶች የታጀበ ነበር።

    ማክሰኞ ዕለት የጋምቢያ የካሳ ኮሚሽን፣ የጃሜህን ንብረት በመሸጥ በአጠቃላይ 2,573,414.10 ዶላር ማግኘቱን “ለተጎጂዎች፣ ከጥቃት በሕይወት ለተረፉ ሰዎች እና ለሕዝቡ ስናሳውቅ በደስታ ነው” ብሏል።

    ገንዘቡ “የተጎጂዎችንና ከጥቃቱ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን መብቶችና ፍላጎቶች በአግባቡ ከግምት ውስጥ በማስገባት” በኃላፊነትና በግልፅነት እንዲተዳደር ቁርጠኛ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

    እአአ በ2016ቱ ምርጫ በአዳማ ባሮው የተሸነፉት ጃሜህ መጀመሪያ ላይ ሽንፈታቸውን ተቀብለው፣ በኋላ ላይ ግን የምርጫውን ውጤት ውድቅ አድርገዋል።

    በመጨረሻም ከቀጣናው አገራትና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጫና በ2017 ከሥልጣናቸው ወርደዋል።

    ሴኔጋልን ጨምሮ ከበርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወታደሮች ጃሜህ ከሥልጣን ካልወረዱ በኃይል ለማስወገድ ወደ ጋምቢያ ተሰማርተው ነበር።

    የኃይል እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ጃሜህ ከሥልጣን ለመውረድ ተስማምተው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ተሰደዋል።

    ጃሜህ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ፣ የቀድሞው ፕሬዝደንት በጋምቢያ 281 ንብረቶች፣ እንዲሁም በአሜሪካ አንድ እና በሞሮኮ አንድ ንብረት እንደነበራቸው የአገሪቱ ብሔራዊ ኮሚሽን አረጋግጧል። በተጨማሪም ከ100 በላይ የባንክ ሒሳቦች ይቆጣጠሩ እንደነበሯቸውም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

    ኮሚሽኑ፣ ጃሜህ ከደመወዛቸው ብቻ ይህን ሁሉ ሀብት ሊያፈሩ እንደማይችሉ በመግለፅ፣ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አላግባብ መጠቀማቸውን ደምድሟል።

    የጃሜህ አገዛዝ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በመግደል፣ ሰዎችን በግዳጅ በመሰወር፣ በመድፈር እና ስቅየትን ያካተቱ ጥሰቶችን በመፈፀም ይከሰሳል።

    የአገሪቱ የምርመራ ኮሚሽንም፣ በጃሜህ ዘመን በሰፊው በተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች “ከ240 እስከ 250 የሚደርሱ ጋምቢያውያን እና ጋምቢያውያን ያልሆኑ ሰዎች በመንግሥት ወይም በወኪሎቹ እጅ” መገደላቸውን አረጋግጧል።

  12. በጎፋ ዞን በአንድ የፖሊስ አባል ግድያ የተጠረጠሩ ከ60 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

    ሚልኪያስ ዳንኤል

    በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ደንባ ጎፋ ወረዳ፣ ሎጤ ቶዣ ስቤ ቀበሌ ውስጥ ረዳት ኢንስፔክተር ሚልኪያስ ዳንኤል መገደላቸውን ተከትሎ ከ60 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የወረዳው የመንግሥት ኮምንኬሽን አስታውቋል።

    የፖሊስ አባሉ የተገደሉት ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 5/2019 ዓ. ም. ከቀኑ 6 ሰዓት ገደማ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የወረዳው ነዋሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በዚሁ ዕለት ለሎጤ ቶዣ ስቤ ቀበሌ የተመደበ ለመብራት አገልግሎት የሚውል ትራንስፎርመር ወደ ሌላ አካባቢ መወሰድ የለበትም በሚል ምክንያት በአካባቢው ነዋሪዎች ረብሻ ተፈጥሮ እንደነበር አንድ የአካባቢው ነዋሪ አስረድተዋል።

    “ሕዝቡ የመብራት ጥያቄ ነበረው፤ መብራት ኃይል ከሕዝቡ ጋር ተነጋግሮ ነበር ሁለት ትራንስፎርመር ወደ አካባቢው የወሰደው። ‘እኛ ብዙ ሕዝብ ነን’ [የኃይል መጠኑ ከፍ ያለው ትራንስፎርመር] ለኛ መግባት አለበት በሚል ነው ግጭቱ የተፈጠረው” ሲሉ አስረድተዋል።

    ነዋሪው አክለውም ሁኔታውን ለማረጋጋት ወደ አካባቢው የተላኩት የፖሊስ አባላት “ትራንስፎርመሩን በመኪና ጭነው ወደ ሳውላ ከተማ ለማምጣት ሲሞክሩ ‘ለኛ ተብሎ የመጣውን ትራንስፎርመር ወደ ኋላ መውሰድ አትችሉም ብሎ ነዋሪው ግጭት ፈጥሮ ሌሎች [የፖሊስ] አባላት በሩጫ አመለጡ” ብለዋል።

    አክለውም “ሚልኪያስ ዳንኤልን በድንጋይ እና በጦር ወግረው ነው የገደሉት” በማለት ክስተቱን አስረድተዋል።

    የረዳት ኢንስፔክተር ሚልኪያስ አንድ የቤተሰብ አባል እንደገለጹት፤ የቀበሌው ነዋሪ ትራንስፎርመሩን በጫነው መኪና እና ፖሊሶች ላይ ድንጋይ መወርወር ከጀመሩ በኋላ ሚልኪያስ ከሌሎች ባልደረቦች ጋር ማምለጥ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

    “ሕዝቡ ሆ ብሎ፣ ግልብጥ ብሎ ወጥቷል፤ ድንጋይ ይዛል። ፖሊስ ላይም፣ ትራንስፎርመሩን በጫነው መኪና ላይም እየወረወሩነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሌሎች የፖሊስ አባላት ወደ ላይ እየተኮሱ ረብሻውን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ከአቅማቸው በላይ ስለነበር እንደሸሹ እኒህ የቤተሰብ አባል ገልጸዋል።

    ይሁን እንጂ ረዳት ኢንስፔክተርሚልኪያስ በድንጋይ እግራቸውን በመመታታቸው ማምለጥ አለመቻላቸውን ገልጸው፣ በተወለዱበት ቀበሌ “በድንጋይ ተደብድበው መገደላቸውን” ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ “የክልሉ ልዩ ኃይል እና የወረዳ ፖሊስ ኃይል ጨምረው እና መሣሪያ ታጥቀው” ወደ ቀበሌው ከገቡ በኋላ አስክሬኑን ማንሳት እንደቻሉ የቤተሰብ አባሉ አክለዋል።

    በወረዳው በኃላፊነት የሚሠሩ አንድ ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በቀበሌው ከመብራት ዝርጋታ ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡ እርስ በእርስ ግጭት ፈጥሮ ነበር።

    ይህንን ግጭት ለማረጋጋት ከተላኩት የፖሊስ አባላት መካከል ረዳት ኢንስፔክተር ሚልኪያስ መገደላቸውን ገልጸዋል።

    ከግድያው ጋር በተያያዘ 62 ተጠርጣሪዎች ተይዘው የፀጥታ አካላት መሰማራታቸውን በመግለጽ በአሁን ወቅት “አንፃራዊ ሰላም ነው” በማለት ወቅታዊ ሁኔታውን አስረድተዋል።

    ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ከሎጤ ቶዣ ስቤ ቀበሌ 62 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።

  13. የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ፑቲንን ለማነጋገር ሩሲያ ሲገቡ፣ ዜሌንስኪ ከአሜሪካ ጋር መረጃ መጋራቱ "አሁን ቀጥሏል" አሉ

    የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዊትኮፍ  እና የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ ኪሪል ድሚትሪየቭ በሴንት ፒተርስበርግ አውሮፕላን ማረፊያ
    የምስሉ መግለጫ, ዊትኮፍ ረቡዕ ጠዋት ሴንት ፒተርስበርግ ሲደርሱ፣ በአውሮፕላን ማረፊያው የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ ኪሪል ድሚትሪየቭ ተቀብለዋቸዋል

    የዩክሬን መሪ፣ ገዳይ የሩሲያ ጥቃቶችን በተመለከተ አሜሪካ የምታደርገው የስለላ መረጃ ማጋራት "አሁን ቀጥሏል" ካሉ በኋላ፣ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን ለማነጋገር ሩሲያ ገቡ።

    ኪየቭ፣ አሜሪካ ከሰሞኑ ለዩክሬን የስለላ መረጃ አለመስጠቷ ዩክሬናውያን ሕይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል ስትል ከሳ ነበር። ዋሽንግተን ግን ይህንን ክስ "አሳፋሪ" ስትል ውድቅ አድርጋዋለች።

    ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ይህንን የተናገሩት ማክሰኞ ዕለት በኦስሎ ከዊትኮፍ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ውይይቱን "ገንቢ" ሲል ገልፆታል።

    የዩክሬን ፕሬዝደንት እና የአውሮፓ አጋሮቻቸው፣ በኦስሎ በተስማሙባቸው ሐሳቦች ላይ ምላሽ መስጠት አሁን የሩሲያ ፈንታ ነው ብለዋል።

    ጦርነቱን ለማቆም በሩሲያ በኩል ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ለመወያየት ዛሬ ረቡዕ ሴንት ፒተርስበርግ የገቡት ዊትኮፍ ከፑቲን ጋር ይገናኛሉ።

    ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም በቅርብ ጊዜ በተካሔዱ የተለያዩ ጥረቶች ላይ እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጡም።

    የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ግን፣ ክሬምሊን ዊትኮፍ የሚያቀርቡትን ሐሳብ እንደሚያዳምጥ ገልፀው፣ "ማንኛውንም ፖለቲካዊ ስምምነት የማድረግ" ዕድልን ግን ውድቅ አድርገዋል።

  14. አውስትራሊያዊቷ የፓርላማ አባል ሆን ተብሎ በተፈፀመባቸው የመኪና ጥቃት ሁለቱንም እግሮቻቸውን አጡ

    ፊል እና ሄለን ሄይንስ
    የምስሉ መግለጫ, ፊል እና ሄለን ሄይንስ ጋብቻ ከመሰረቱ 40 ዓመት ያህል ሆኗቸዋል፤ በቀጣዩ ወር 40ኛ ዓመት የጋብቻ ክብረበዓላቸው ያከብራሉ

    ባለሥልጣናት ሆን ተብሎ የተፈፀመ ጥቃት ነው ባሉት ክስተት በመኪና የተገጩት የአውስትራሊያ የምክር ቤት አባል ሔለን ሄይንስ ሁለቱንም እግሮቻቸውን ማጣታቸውን ባለቤታቸው አረጋገጡ።

    ፊል ሄይንስ፣ ይህ "አሰቃቂ ክስተት" ባለቤታቸው ከባድ ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉን ገልፀው፣ "ልቧ እና አእምሮዋ ግን በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው" ብለዋል። "በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ያለው መልካም ዜና በሕይወት መኖሯ ነው" ሲሉም አክለዋል።

    ጥቃቱን በመፈፀም የተጠረጠረው የ43 ዓመቱ ብሬንዳን ኑገንት፣ ከጥቃቱ ጋር በተያያዙ የተለያዩ ወንጀሎች ተከስሶ ረቡዕ ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

    ኑገንት ሰኞ ዕለት በቶዮታ ላንድክሩዘር መኪናው ገለልተኛዋን የፓርላማ አባል ሄይንስን ከገጨ በኋላ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

    ግለሰቡ ጥቃቱን የፈፀመው፣ ከሜልቦርን በስተሰሜን ምሥራቅ 240 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ዋንጋራታ ከተማ ውስጥ የሄይንስ የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት መግቢያ አካባቢ ነው።

    ለሄይንስ ሕክምና እየተደረገ ባለበት ሜልቦርን በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "ወደ ጤናዋ የምትመለስበት ጉዞ ረዥምና አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሄይንስ የማትበገር መሆኗን እናውቃለን" ሲሉ ባለቤታቸው ተናግረዋል።

    "እሷ ቆራጥ ሰው ነች። የእኛ ድጋፍና ፍቅር ታክሎበት ለማገገም የቻለችውን ሁሉ እንደምታደርግ እናውቃለን። ተስፋ የምናደርገውም ይህንኑ ነው" ሲሉም አክለዋል።

    ባለቤታቸው የሆስፒታሉን ሠራተኞች፣ እንዲሁም በአውስትራሊያና በሌሎች አገራት ለሄይንስ መልካም ምኞታቸውን የገለፁ ሰዎችን አመስግነዋል። ድጋፋቸውን በገንዘብ ማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች በህጻናት ላይ ለሚሰራው ዓለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) መዋጮ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

    የመኪና ጥቃቱን የፈፀመው ኑገንት ሦስት ክሶች የተመሰረቱበት ሲሆን፣ ክሶቹም ከባድ ጉዳት ያደረሰ አደገኛ የመኪና አነዳድ፣ ሆን ብሎ ከባድ ጉዳት ማድረስ እና በመንግሥት ባለሥልጣን ላይ ጉዳት ማድረስ የሚሉ ናቸው።

    የግድያ ሙከራን ጨምሮ ተጨማሪ ክሶች ሊቀርቡበት እንደሚችሉም ፖሊስ ገልጿል።

  15. ሩሲያ ለዩክሬን ሲዋጋ ይዤዋለሁ በማለት ያሰረችውን አሜሪካዊ መልቀቋ ተሰማ

    የ74 ዓመት አሜሪካዊ ስቴፈን ሃባርድ
    የምስሉ መግለጫ, የ74 ዓመት አሜሪካዊ ስቴፈን ሃባርድ

    ሩሲያ ለዩክሬንን ሲዋጋ ይዤዋለሁ በማለት ያሰረችውን የ74 ዓመት አሜሪካዊ ለመልቀቅ መስማማቷን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መናገራቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ፑቲን ከአሜሪካው አምባሳደር ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በሴንት ፒተርስበርግ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ስቴፈን ሃባርድ ወደ ፑልኮቮ አውሮፕላን ማረፊያ ተወስዷል ብለዋል።

    መምህር እና የሚቺጋን ነዋሪ የነበረው ሃባርድ እአአ በ2024 ለዩክሬን ተሰልፎ ተዋግቷል ተብሎ ከተከሰሰ በኋላ ሰባት ዓመት ተፈርዶበታል።

    አቃቤ ሕግ ሞስኮ ከሁለት ዓመት በፊት ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረች በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምሥራቅ ኢዚየም ከተማ በሚገኝ የዩክሬን መከላከያ ዕዝ ውስጥ ሲያገለግል ነበር በሚል ከሶታል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ሲል ሃባርድን "በስህተት ታስሯል" ያለ ሲሆን ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በግለሰቡ ዙሪያ ከፑቲንጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ለጋዜጠኞች "ምን እንደሚሆን ተመልከቱ፤ ትኩረታችን በሃባርድ ላይ ነው" ብለዋል።

    የቢቢሲ የአሜሪካ የሚዲያ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ሃባርድ የጤና እክል እንዳለበት እና ለሕክምና ወደ ቴክሳስ እንደሚወሰድ ዘግቧል።

    ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከዋይት ሐውስ አስተያየት ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

  16. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ሦስት ቦታዎች መለየታቸውን ተናገሩ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን ሲጎበኙ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ከ30 በላይ ቦታዎች ሲጠኑ መቆየታቸውን ገልጸው ሦስት ቦታዎች መለየታቸውን አስታወቁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ዛሬ ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ አሁን ላይ የጥናት ቡድን ተዋቅሮ፣ ተቋሙ በሕግ ተመሥርቶ፣ መሪዎች እና ባለሙያዎች ተመድበውለት፣ እንዲሁም የቢሮ እና የሰው ሀብት ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ሙሉ ተቋማዊ ቁመና መያዙን ተናግረዋል።

    አክለውም የኒውክሌር ፕሮጀክቱ የሚገነባበትን ቦታ ለማመቻቸት በሙያተኞች ከ30 በላይ ቦታዎች ሲጠኑ መቆየታቸውን ገልጸው፤ የጥናቱ ሂደት ደረጃ በደረጃ ወደ ሦስት ቦታዎች መለየታቸውን ይፋ አድርገዋል።

    “ከ30 ወደ 13 ገደማ፣ ከዛ አምስት ከዚያ ሦስት እያሉ ቦታ ለይተዋል፤ እነዚህን ቦታዎች እኛ ‘አፕሩቭ’ ማድረግ [ማጽደቅ] አንችልም” በማለት የውጭ ተቋማት የቦታውን አዋጭነት እና ለግንባታው ምቹነት ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

    የቦታው ምቹነት ከተረጋገጠ በኋላ ቦታውን የማዘጋጀት፣ ቴክኖሎጂውን ከሚሰጥ ተቋም ጋር ስምምነት መፈራረም እንደሚኖር ተናግረዋል።

    ሥራው እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንዴ ኮንትራት ተሰጥቶ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ አለመሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በርካታ ተቋማትን እና ዲፓርትመንቶችን የሚነካ፣ ሰፊ የሰው ሀብት እና ዝግጅት የሚጠይቅ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

    የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽንን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ሌሎች ኃላፊዎች ጋር በመሆን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስልታዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

    ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ እንደምትታወቅ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ምዕራፍ ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ እንደሚጀመር ይፋ ያደረጉት ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ነበር።

    የኃይል ማመንጫ ግንባታውን ይፋ ባደረጉበት ወቅትም "ለሰላማዊ" ዓላማ ብቻ የሚውል እንደሆነም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ልትገነባው ያቀደችው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ምንድን ነው?

    የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ውስጥ የተዘጋጀ ዐውደ ርዕይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ለአገሪቱ የረዥም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማዕከላዊ በመሆኑ፣ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ሲሉም ተናግረዋል።

    ቴክኖሎጂው ከኃይል ምርት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለአገራዊ ልማት መሠረታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል።

    ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት ውስጥ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ዩኒቶችን ለመገንባት ዕቅድ እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

    ይህ በድምሩ 2 ሺህ 400 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የታቀደው ፕሮጀክት፣ እንደ ውኃ፣ ፀሐይ እና ነፋስ ኃይል በወቅቶች መፈራረቅ አቅሙ የማይዋዥቅ በመሆኑ፣ ዓመቱን ሙሉ ወጥ በሆነ አቅም በሚያመርተው የኃይል መጠን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደሚበልጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

    "በእኛ ሁኔታ የምንፈልገው ሁለት ዩኒት እያንዳንዱ 1200 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ነው። ይህንን ለመስራት በጣም ከፈጠንን አስር ዓመት ይፈጃል"።

    የኒውክሌር ኢንቨስትመንት የመጀመሪያ ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም፣ አንዴ ከተገነባ ከ60 እስከ 100 ዓመታት የሚዘልቅ እና ለትውልድ የሚተርፍ ፕሮጀክት ነው ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

  17. ኤለን መስክ ቴስላን እና ስፔስ ኤክስን ለማዋሃደ እያሰበ መሆኑን ተናገረ

    ኤለን መስክ

    ኤለን መስክ ሁለቱን ትላልቅ ኩባንያዎቹን፣ ቴስላን እና ስፔስ ኤክስን፣ ለማዋሃድ እያሰበ መሆኑን ተናገረ።

    መስክ ከፋይናንስ ተንታኞች ጋር ማክሰኞ ዕለት በነበረው የስልክ ውይይት “ጥሩ ሃሳብ ነው ብዬ አስባለሁ? አዎ” ሲል ተናግሯል።

    ኤለን መስክ ውህደቱ እርግጠኛ እንዳልሆነና የአክሲዮን ባለቤቶችን ይሁንታ እንደሚፈልግ ተናግሯል። ሆኖም፣ ሁለቱም ኩባንያዎች ሀሳቡን ለመመርመር ልዩ ኮሚቴዎችን ማቋቋማቸውን ገልጿል።

    መስክ አክሎም፣ ልዩ ኮሚቴዎቹ በስምምነቱ ውሎች ላይ እስካሁን ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን እና ስምምነት ላይ እንደሚደርሱም ምንም ዓይነት ዋስትና እንደሌለ አስረድቷል። ሆኖም ውህደቱ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ገልጾ ከፍተኛ ትርፍንም ሊያስገኝ ይችላል ብሏል።

    ቴስላ በግምት 1.5 ትሪሊዮን ዶላር፣ ስፔስ ኤክስ ደግሞ 2 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ሲሆን፣ እነዚህን ሁለት ኩባንያዎች ከተዋሃዱ በታሪክ ውስጥ ከተከናወኑ ትላልቅ ውህደቶች አንዱ ይሆናል።

    የስፔስ ኤክስ አክሲዮኖች መደበኛ የገበያ ሰዓት ካለቀ በኋላ በተካሄደ ግብይት 8 በመቶ ጨምረዋል።

    የጠፈር ሮኬቶችን እና የ’ስታርሊንክ’ የኢንተርኔት ሳተላይቶችን የሚያመርተው ይህ ኩባንያ፣ አገልግሎቱን በማስፋፋት እንደ ‘አንትሮፒክ’ እና ‘ጉግል’ ላሉ ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች 'የኮምፒውቲንግ' አቅም ማቅረብ ጀምሯል።

    የቴስላ አክሲዮኖች ለተወሰኑ ሳምንታት ዋጋቸው በመጠኑ ቀንሶ ከቆየ በኋላ፣ አሁን በ2 በመቶ ከፍ ብሏል። ​​ኩባንያው የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን ረቡዕ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

    ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ መስክ የራሱ የሆኑ ኩባንያዎችን በማሰባሰብ በጥቂት የኮርፖሬት ቡድኖች ስር እያደራጃቸው ይገኛል።

  18. የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥሪ አቀረቡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ለትራምፕ ባደረጉት የስልክ ጥሪ እስራኤል እና አሜሪካ ኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ሊከፍቱ እንደሚችሉ አመላከቱ።

    በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በተሠራጨው የስልክ ንግግር ኔታኒያሁ በሚቀጥለው ሳምንት ለሚካሄደው የእስራኤል ብሔራዊ ምርጫ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሰጧቸው የምርጫ ድጋፍ አመስግነዋል።

    ምርጫው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከጥቅምቱ የሀማስ ጥቃት በፊት እና በኋላ እንዲሁም የኢራን ጦርነትን ጨምሮ ተከታታይ ጦርነቶች ላይ ያሳዩት መሪነት ላይ የሚሰጥ “ሕዝበ ውሳኔ” እንደሆነ በስፋ የሚታመን ሲሆን፤ ከባድ ፉክክር እንደሚገጥማቸውም ይጠበቃል።

    “ዶናልድ መጨረስ ያለብን ሥራ አለ። አንተ እንዳልከው በጋራ እንጨርሰዋለን። እንጨርሰዋለን፤ ሌላ ማንም ሊያደርገው አይችልም” ሲሉ ኔታኒያሁ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአሜሪካ የመካከለኛ ዘመን ምርጫ በፊት ኢራን ላይ አዲስ ጥቃት እንደማይፈፅሙ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት ሁለቱ መሪዎች አዲስ የጥቃት ዘመቻ ለመክፈት መነጋገራቸውን አክሲዮስ የተባለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    ሦስት ምንጮችን የጠቀሰው አክሲዮስ የመሪዎቹ ንግግር የተደረገው ትራምፕ የመካከለኛ ዘመን የአሜሪካ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፅሙ ከመናገራቸው በፊት ነው።

    የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን ሁለቱ መሪዎች ጦርነቱን ዳግም ለመጀመር ተነጋግረዋል መባሉን “ውሸት” ብለውታል። ለዚህም የጠቀሱት ትራምፕ በኅዳር ከሚደረገው ምርጫ በፊት ጥቃት መፈፀሙን ውድቅ ማድረጋቸውን ነው።

    የሁለቱም አገራት ወታደሮች በተጠንቀቅ ሲሆኑ ትራምፕ አቋማቸውን ከቀየሩ በሚል ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ እንደሆነም ምንጩ ተናግረዋል።

  19. የሁቲ ታጣቂዎች በየመን ካምፕ ላይ በፈፀሙት የሚሳኤል ጥቃት 73 ምልምል ወታደሮች ተገደሉ

    ፎቶ ከፋይል
    የምስሉ መግለጫ, የየመን መንግሥት በጥቃቱ የተገደሉት ለአገር ውስጥ የፀጥታ አስከባሪነት እየሰለጠኑ የነበሩ ምልምሎች መሆናቸውን አስታውቋል

    በየመን ማዕከላዊ ግዛት ሻባዋ ሰኞ ዕለት በሁቲ ታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት ከ70 የሚበልጡ ምልምል ወታደሮች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    በሳዑዲ የሚደገፈው የየመን መንግሥት ጦር ኃይሎች እንዳስታወቀው የሁቲ አማፂያን በአዋቅ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አል-አላም ካምፕ ሦስት ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ተኩሰዋል። ካምፑ የፀጥታ ኃይል እና የፖሊስ ምልምሎች ማሰልጠኛ ማዕከል በመሆን የሚያገለግል መሆኑንም ገልጿል።

    የየመን ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት መሪ ረሽድ አል-አሊሚ “የወንጀል ጥቃት” ያሉትን ጥቃት አውግዘው “ጠንካራ እርምጃ” እንደሚወሰድ ቃል ገብተዋል።

    የሁቲዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ “የሳዑዲ ጠላት ስብስብ” ዒላማ መደረጉን ተናግረዋል።

    ከሳምንታት በፊት የመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች በምዕራባዊ የመን በሁቲ የተያዙ ግዛቶችን ለመቆጣጠር ትልቅ ዘመቻ ከፍተዋል።

    በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምር የአረብ አገራት የአየር ድጋፍ በመታገዝ በቀይ ባሕር ዳርቻ ባለፈው መስከረም ሁቲዎች በድንገት የያዟቸውን አካባቢዎች መቆጣጠር ችለዋል።

    ይሁን እንጂ በአካባቢው እና በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባለችው ቲያዝ ከተማ እና በማቲብ እና አል-ጃዋፍ ግዛቶች ጠንካራ ውጊያዎች ቀጥለዋል።

    ሁቲዎች ሳዑዲ ለፈፀመችው የአየር ጥቃት በአየር ማረፊያዎች፣ በኃይል ጣቢያዎች እና በወታደራዊ ሰፈሮች የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን በመፈፀም ምላሽ ሰጥተዋል።

    በሻባዋ የተፈፀመው የሰኞው ጥቃት ጦርነቱ ከተባባሰ በኋላ እጅግ ገዳይ ጥቃት እንደሆነ ተዘግቧል።

    የግዛቱ የሚዲያ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የባላስቲክ ሚሳኤሉ ከተለያዩ ግዛቶች የአገር ውስጥ የፀጥታ መኮንኖች ለመሆን የተሰባሰቡ ምልምሎች በሚሰለጥኑበት ማዕከል የተፈፀመ ነው ብሏል።

    በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በካምፑ የወዳደቁ አስከሬኖች አሳይተዋል።

    የሚዲያ ቢሮው መጀመሪያ ላይ 53 ሰዎች መገደላቸውን እና 200 የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውን አሳውቆ ነበር።

    በማግሥቱ በወጣ አዲስ መግለጫ የሟቾች ቁጥር 73 መድረሱን እና ተጨማሪ 14 ሰዎች የገቡበት አለመታወቁ ተገልጿል።

  20. አሜሪካ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ300,000 በላይ ቪዛዎችን መሰረዟን አስታወቀች

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከ300,000 በላይ ቪዛዎችን መሰረዛቸውን አስተዳደራቸው አስታወቀ።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ300,000 በላይ ቪዛዎችን መሰረዙን ማክሰኞ ዕለት ያስታወቀው የፌዴራል መንግሥቱ በስደተኞች ላይ የሚያደርገውን ሰፊ ​​የቁጥጥር እርምጃ አጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።

    ይህ ቁጥር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቪዛ የመሰረዝ ሂደቱ በከፍተኛ ሁኔታ መፋጠኑን ያሳያል።

    “ከ300,000 በላይ ቪዛዎች ተሰርዘዋል፤ ቁጥሩም እየጨመረ ነው። ለቪዛ ባለቤቶች ያለን መልዕክት ቀላል ነው፤ ሕጎቻችንን አክብሩ፤ አለበለዚያ ወደ አሜሪካ የመጓዝ መብታችሁን ታጣላችሁ” ሲሉ የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቆንስላ ጉዳዮች ረዳት ጸኃፊ ሞራ ናምዳር በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    “ለፕሬዚዳት ትራምፕ እና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ አገራችንን እና ሕዝባችንን መጠበቅ ዛሬም ሁሌም ቀዳሚው ነገር ነው” ሲሉም አክለዋል።

    ኃላፊዋ በገጻቸው ላይ ዋይት ሐውስ “የትራምፕ አስተዳደር በታሪክ ከነበሩ አስተዳደሮች ሁሉ በበለጠ ፍጥነት እና ብዛት ቪዛዎችን ሰርዟል” በማለት የለጠፈውን መልዕክት አጋርተዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ቶሚ ፒጎት በኤክስ ገጻቸው ላይ ቪዛቸው የተሰረዘው ውጭ ዜጎች በሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ለይ የተሳተፉ ወይም ለብሔራዊ ደህንነት አደጋ የደቀኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።

    “እዚህ ቪዛ ኖሯቸው ሕግን የሚጥሱ፣ ማጭበርበር የሚፈጽሙ ወይም ብሔራዊ ደህንነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ የውጭ ዜጎችን በፍጹም አንታገስም” ብለዋል።

    ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው የትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ከ175 ሺህ በላይ ቪዛዎች መሰረዛቸውን አስታውቆ ነበር።

    አሁን ይፋ የሆነው ቁጥር በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቪዛዎች መሰረዛቸውን የሚያሳይ ነው።

    ትራምፕ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞችን ወደ መጡበት አገር ማባረር የአገር ውስጥ ደህንነትን ለማሻሻል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።