ኢራን እና ፓኪስታንን ጨምሮ የአራት አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቴህራን በጋራ እየመከሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, IRIB
የኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ከፍተኛ ሹማምንት በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በቴህራን ንግግር ጀመሩ።
አሜሪካ እና ኢራንን እያደራደሩ ያሉት የፓኪስታን ጦር ኃይሎች አዛዥ አሲም ሙኒር፣ የሳዑዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሰልማን እና የቱርክ የደኅንነት አለቃ ኢብራሂም ካሊን በቴህራን የጋራ ምክክሩ ላይ ተገኝተዋል።
የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እና ከፍተኛ የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ፀሐፊ ሞሸን ራዚያ የኢራንን ልዑክ ወክለው በስብሰባው ከተገኙት መሀል ናቸው።
ሳዑዲ አረቢያ ከስብሰባው ቀደም ብላ ባወጣችው መግለጫ የምክክሩ ግብ ግጭት እንዳይባባስ ማድረግ እና ለስምምነት መንገድ መጥረግ ነው ብላለች።
ሳዑዲ፣ ፓኪስታን እና ቱርክ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ “የመካ ስምምነት” የተባለ የመከላከያ እና ደኅንነት አጋርነት ፈርመዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እንዳይባባስ ማድረግ “ወሳኝ ነው” ብለዋል።
ዋና ፀሐፊው በካይሮ በሰጡት መግለጫ እየጨመረ ስለመጣው የአሜሪካ ዛቻ እና ከኢራን ጋር ሊኖር ስለሚችል ስምምነት በተመለከተ፤ በኢራን እና በገልፍ አገራት ሊቀሰቀሱ የሚችሉ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃቶችን “በየትኛውም ዋጋ” መከላከል ያስፈልጋል ሲሉ አስምረዋል።
ጉቴሬዝ ይህን ያሉት የሳዑዲ፣ ቱርክ እና ፓኪስታን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኢራን ለመነጋገር ቀን ከቆረጡ በኋላ ነው።









