የኔፓል ጎርፍ ከመከሰቱ ከደቂቃዎች በፊት 900 ልጆችን ያስመለጠው ርዕሰ መምህር

ሰማያዊ ሸሚዝ የለበሰ ሰው ብርትኳናማ እና ነጭ ቀለም ካለው መጋረጃ ፊት ለፊት ቁጭ ብሎ ሲያወራ
የምስሉ መግለጫ, ራጄንድራ ዳዋዲ፣ የጎርፉ ውሃ ወደ ትምህርት ቤቱ እያመራ ስለመሆኑ ማስጠንቀቂያ እንደደረሰው ነበር ፈጣን እርምጃ መውሰድ የጀመረው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር፣ ከ900 በላይ ሰዎችን የገደለው የኔፓል ጎርፍ ከመከሰቱ ከ10 ደቂቃዎች በፊት 900 ተማሪዎች በፍጥነት ለቅቀው እንዲወጡ በማድረግ የተማሪዎቹን ሕይወት መታደግ ችሏል።

በኑዋኮት የሚገኘው የትሪብሁቫን ትሪሹሊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ራጄንድራ ዳዋዲ፣ ተማሪዎቹን እንዴት እንዳዳነ ለቢቢሲ ሲያብራራ፣ ጠዋት 3፡10 ላይ ስለ አደጋው የሚያስጠነቅቁ ሦስት የስልክ ጥሪዎች እንደደረሱት ገልጿል።

ከዚያም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ቦታዎች ሩጠው እንዲወጡ፣ ተማሪዎችን ጭነው ወደ ትምህርት ቤቱ በማምራት ላይ የነበሩ አውቶቡሶችም ፊታቸውን አዙረው ከስፍራው እንዲያመልጡ በማዘዝ አስቸኳይ እርምጃ መውሰዱን ተናግሯል።

"ፈጣን እርምጃ ባንወስድ ኖሮ፣ 10 ደቂቃ እንኳን ዘግይተን ቢሆን እኔን እና ተማሪዎቹን ጨምሮ ሁላችንም ዛሬ ከእናንተ ጋር ልናወራ አንችልም ነበር" ይላል ዳዋዲ ሁኔታውን ሲያስረዳ።

እየተቃረበ ያለውን አደጋ በመገምገም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ያስቻሉት ማስጠንቀቂያዎች በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ከአራት ሰዎች እንደደረሱት ገልጿል።

"አንድ ወላጅ መጥቶ 'ከባድ ጎርፍ እየመጣ ነው ልጄን ልወስዳት ነው የመጣሁት፤ እወስዳታለሁ' አሉኝ" ሲል አክሏል።

"ጠንካራ ምክንያት ሳይኖራቸው ወላጆች እንዲህ አይጣደፉም፤ ስለዚህ ልጆቹን ለማውጣት አንድም ሰከንድ ማባከን የለብኝም" በማለት ወሰነ።

"ምንም መዘግየት የለብኝም ብዬ ወሰንኩ። ጎርፍ ባይመጣም እንኳን፣ የአንድ ቀን ትምህርት ነው ሊቀር የሚችለው" በማለት ፈጣን ርምጃውን ወሰደ። በዚህም "የብዙዎችን ህይወት በማትረፋችን ኩራት ይሰማናል" ይላል።

የኔፓልን የተወሰነ ክፍል ባጠቃው ጎርፍ እስካሁን 903 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ ቢያንስ 4,247 ሰዎች ጠፍተዋል።

ጎርፉ ትምህርት ቤቱን በደለል እና በፍርስራሾች ቀብሮታል።

ከወንዙ 100 ሜትር ርቀት ላይ ያ የሆቴል ህንጻን በፍጥነት ያወደመው ድንገተኛው ጎርፍ፣ እጅግ በፍጥነት ሲጓዝ እንደነበር ዳዋዲ ተናግሯል።

መጀመሪያ ላይ በርካታ ተማሪዎች ስለሁኔታው ከባድነት አላወቁም ነበር።

ጥቁር ልብስ የለበሰች ባለ ጥቁር ፀጉር ልጅ ከበር ፊት ለፊት ቁጭ ብላ ኢንተርቪው እየተደረገች
የምስሉ መግለጫ, የ16 ዓመቷ ተማሪ ዩኒሻ አማትያ ጎርፍ አደጋውን በቅጽበት ማምለጥ ችላለች

ዩኒሻ አማትያ የተባለች የ16 ዓመት ተማሪ፣ ጎርፉ ከመከሰቱ በፊት ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ስፍራ ከጓደኞቿ ጋር በፍጥነት ተሯሩጣ ማምለጧን አስረድታለች።

"እኔ እና ጓደኞቼ በ10 ሰከንድ ልዩነት ነው የተረፍነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ጎርፉ ከመምጣቱ በፊት ክፍል ውስጥ እየተማርን ነበር። መምህራን አንድ ቦታ ላይ ተሰባሰቡ፤ ምን እንደተፈጠረ መጀመሪያ ላይ አላወቁም ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ መምህራን ወደ እኛ መጡና ስለጎርፉ መረጃ ሰጥተውን ወደቤታችን እንድንሔድ ነገሩን" ብላለች።

ስለአደጋው ከሰማ በኋላ አንድ ተማሪ ራሱን ስለመሳቱ የተናገረችው ዩኒሻ፣ ብዙዎቹ ግን አደጋውን አሳንሰው ተመልክተው እንደነበረ እና ሂሳብ ሲማሩ የነበሩ ጓደኞቻቸውን ሲጠብቁ እንደነበር አብራርታለች።

እርሷና ጓደኞቿ ግን ጊዜ ሳያጠፉ ወዲያው በትምህርት ቤቱ የኋላ በር በኩል ባለች መውጫ ተሯሩጠው ከፍ ወዳለ ስፍራ መሔዳቸውን አክላለች።

"በቅጽበት ዐይኔ እያየ የደመቀው መንደር ተጠርጎ ተወሰደ" ትላለች በትምህርት ቤቱ ዙሪያ በነበረው የገበያ ስፍራ ላይ የተከሰተውን ድንገተኛ አደጋ ስታብራራ።

አክላም "ጫማዬ መቆንጠጫ ባይኖረው ኖሮ እወድቅ ነበር። ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ስፍራ ለማምለጥ ሲሯሯጡ ይገፋፉ ነበር። በሌላ አቅጣጫ ለማምለጥ የሞከሩ [በጎርፉ] ሳይወሰዱ አልቀሩም" ብላለች።

ተማሪዎቹ እና መምህራን ወደ አጎራባች መንደሮች ከማቅናታቸው በፊት ጥቂት መቶ ሜትሮች ከፍታ ወዳለው ስፍራ ነበር ያቀኑት። መንገዶች በመጎዳታቸው እና የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ፣ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እስኪደርሱላቸው ድረስ ሁለት ምሽቶችን በስፍራው አሳልፈዋል።