'ካሳ ስለከፈልኩብሽ ታገቢኛለሽ'፡ በግፍ የተገደለችው የሴቶች መብት ተሟጋቿ መሰለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ማሳሰቢያ፦ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ይዘት አለው።

መሰለች ካሽንቴት 23 ዓመቷ ነበር። ተስፋዋን፣ ሕልሟን፣ የሕይወት ውጥኗን ሳትሞላ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላለች።

ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ. ም. ነው፤ የምርቃት ድግሷ ሁለት ቀናት ቀርተውታል። ለድግሱ ሸመታ ገበያ ወጣች።

አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ በግድያዋ ተጠርጣሪ የሆነው ግለሰብ ገጀራ ይዞ ወደ መሰለች ማምራቱ ተገልጿል። ቢቢሲ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ማንም አላስቆመውም፤ ጩኸቷም ሰሚ አላገኘም።

መሰለች የዚያኑ ዕለት በገጀራ ተገድላ አስከሬኗ ተገኝቷል። ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

መሰለች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በቤንች ሸኮ ዞን፣ ሰሜን ቤንች ወረዳ፣ ቃሻ ቀበሌ ትኖር ነበር።

በቃሻ ቀበሌ የንቃት ወጣቶች ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ እና የሴቶች ጥቃት ተከላካይ ቡድን ፀሐፊ ነበረች። ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ትታወቃለች።

ጠለፋ እና ድርብ ጋብቻ በስፋት በሚስተዋልበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሴቶች መብት ተሟጋች በመሆን ስሟ ይነሳም ነበር።

ነገር ግን ስትታገላቸው የነበሩት ድርጊቶች ተፈጽመውባታል። በድርብ ጋብቻ ውስጥ አልገባም ስላለች ተጠልፋለች፣ በስተመጨረሻም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላለች።

የመሰለችን ግድያ በተመለከተ ቢቢሲ ከአክሽን ኤድ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች እና ከአርቲክል 35 መረጃ አግኝቷል። የቤንች ሸኮ ዞን የፍትሕ መምሪያ፣ ተጠርጣሪው ፍቃዱ ግሽናር ፍርድ ቤት መቅረቡን ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ሦስቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ መሰለች ከመገደሏ በፊት ተደራራቢ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደደረሰባት አስታውቀዋል።

ነገሩን ከሥር ከመሠረቱ ለመረዳት ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ወደኋላ እንመለስ።

በመሰለች ግድያ የተጠረጠረው ግለሰብ ባለ ትዳር እና የአራት ልጆች አባት ነው። መሰለች እንድታገባው ሲጠይቅ ድርብ ጋብቻ ውስጥ እንደማትገባ አስታወቀች።

ይህንን ተከትሎ ግለሰቡ መሰለችን በመጥለፉ ጉዳዩን ወደ ሕግ አካል ወስዳው ነበር። ነገር ግን በአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብነት ሕጋዊ መፍትሔ ሳታገኝ ቀርታለች።

በኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች የሥርዓተ ፆታ እኩልነት እና አካቶ ትግበራ ኃላፊ የሆነችው ዮርዳኖስ ጌታሁን፣ ከመሰለች ጋር የተዋወቀችው በሰሜን ቤንች ወረዳ የሴቶች መብት ንቅናቄ ስታደርግ ነው።

የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች ከአክሽን ኤድ ኢትዮጵያ ጋር በሚያካሂደው ንቅናቄ የፆታዊ ጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ አዋቅሮ መሰለች ፀሐፊ ነበረች።

በአካባቢው ድርብ ጋብቻ እና ጠለፋን የመሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቅረፍ ጥረት የምታደርገው መሰለች ስትጠለፍ የኮሌጅ ተማሪ እንደነበረች ዮርዳኖስ ትናገራለች።

"የጋብቻ ጥያቄ ያቀርብ ነበር። ድርብ ጋብቻ ውስጥ አልገባም የሚል ነበር ምላሿ።"

እምቢታዋን አልፎ ሲጠልፋትም "ጠለፋውን አምልጣ ወደ ቤተሰቧ እንደተመለሰች እና ጉዳዩ በሕግ እንደተያዘ" ትናገራለች።

የቤንች ሸኮ ዞን ፍትሕ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች የሥራ ሒደት አስተባባሪ የመምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ኤፍሬም ዲጊቶ "የጠለፋ ሙከራ አድርጎ በወረዳ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት የአገር ሽማግሌ ጣልቃ ገባ" ሲሉ ይገልጻሉ።

ዮርዳኖስ እንደምትለው፤ በሕግ ጉዳዩ ተይዞ ሳለ መሰለች ላይ በሽማግሌ ጫና ተደርጎባታል። ግለሰቡም "ካሳ እንዲከፍል" እና መሰለች ክስ እንድታቋርጥ በሽማግሌዎች ተወሰነ።

አቶ ኤፍሬም እንደተናገሩት፤ መሰለች ካሳውን እንድትቀበል እና "ፍርድ ቤት ሄዳ ቃሏን እንድትቀይር" ተደርጋለች።

በደረሰባት ተጽዕኖ ምክንያት "ሊጠልፈኝ አይደለም። ቤተሰቦቼን ከርቀት አይቼ ነው ደንግጬ የጮህኩት" ለማለት ተገድዳለች።

"ጠለፋም ድርብ ጋብቻም ወንጀል ነው" የምትለው ዮርዳኖስ፤ የወንጀል ክሱ "ከሳሽ አቁሜያለሁ ስላለች ብቻ መቋረጥ አልነበረበትም። ግን ተቋርጧል" ስትል ታስረዳለች።

ግለሰቡ "ከጠለፋ ሙከራ" ክስ ነጻ መውጣቱን አቶ ኤፍሬም ይገልጻሉ።

ይባስ ብሎ መሰለች መጀመሪያ ላይ ለፖሊስ የሰጠችውን ቃል "ስለለወጠች" ታስራ ከተወሰነ የምርመራ ሒደት በኋላ መለቀቋን ያስረዳሉ።

"ፍርድ ቤት ሄዳ [ቃሏን] ከቀየረች ወይ መጀመሪያ የሐሰት ክስ አቅርባለች በሚል ዐቃቤ ሕግ ደብዳቤ ጽፎ፣ ታስራ፣ ከተወሰነ ሒደት በኋላ ነው የቀረው።"

ግለሰቡ የሰጠው ካሳ "28 ሺህ ብር" እንደሆነ የክስ መዝገቡ እንደሚያሳይ ይናገራሉ። ይህም "የእርቅ የውል ስምምነት" ተብሎ የተመዘገበ ነው።

ዮርዳኖስ እንደምትለው፤ ግለሰቡ ካሳ መክፈሉን "እንደ አስገዳጅ ሁኔታ" በመውሰድ "ካሳ ከፍዬብሻለሁ፣ እኔን ልታገቢኝ ግድ ነው" በሚል ዛቻ እና ማስፈራሪያ ያደርስባት ነበር።

"እንኳን ለራሴ ለሌሎች ሴቶችም የምቆም ነኝ በሚል ቦታ አልሰጠችውም። ለምርቃቷ እየተዘጋጀች ሳለ ገበያ በወጣችበት ነው ከገበያ መሀል እየተጎተተ ወስዶ የገደላት።"

መሰለች የተገደለችው ቅዳሜ ልትመረቅ ሐሙስ ዕለት ነበር።

ከ2016 ዓ.ም. አንስቶ ሲከታተላት "ምንም ለውጥ አይመጣም" በሚል በድጋሚ ወደ ፖሊስ አልሄደችም።

በፍትሕ አካላት በኩልም የመጀመሪያውን ክስ አቋርጣለች በሚል እሷን "ወደ መውቀስ አዘንብለው" ነበር።

የፆታ እኩልነትን ለማስፈን የሚንቀሳቀሰው አርቲክል 35 መሥራች ኪያ ዓሊ እንደምትለው፤ ተጠርጣሪው "ከገበያ መሀል ገጀራ ይዞ እየጎተተ ሲወስዳት በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረው የተሳሳተ አመለካከት 'ካሳ ከፍሎባታል ሚስቱ ናት፣ እንደፈለገ ሊያደርጋት ይችላል፣ ሊወስዳት ይችላል" የሚል ነበር።

በአካባቢው ልማድ ገበያ የሚቆመው አመሻሽ ላይ ነው። ተጠርጣሪው መሰለችን ከገበያ "እየጎተታት ሲሄድ" የዐይን እማኞች እንደነበሩም ዮርዳኖስ እና ኪያ ይናገራሉ።

"ካሳ ከፍሎባታልና የእሱ ናት" በሚል ጣልቃ የገባም አልነበረም።

ለመጮህም፣ ለማስጣልም እንዳልተሞከረ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ ያስረዳሉ።

አቶ ኤፍሬም እንደሚሉት፤ ተጠርጣሪው መሰለችን የያዘው "ከጓደኞቿ ጋር ከገበያ እየተመለሰች" ሳለ ነው።

"ሌላ ሰው ልታገባ ነው የሚል ሲሰማ በምታልፍበት በመንገድ ላይ ጠብቆ አገኛት። ከእሷ ጋር የነበሩትን በገጀራ አስፈራርቶ አሳድዷቸው ሮጡ። እሷን ይዞ ሄዶ በገጀራው ቆረጣት።"

ተጠርጣሪው ገጀራ ይዞ መሰለችን ለመያዝ ሲሞክር ሌሎች ሰዎች ሲጮሁ አምልጣ ብትሮጥም እንደያዛት ይናገራሉ።

"በሮጠችበት ተከትሎ [ከገበያ ሥፍራው] ትንሽ ገባ ባለ ቦታ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ቆረጣት። ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ነው። ድንጋይም ራሷ ላይ ከመረባት። ገጀራውን እዛው ጥሎ አመለጠ። ከአካባቢው ሸሽቶ የዚያኑ ቀን ምሽት ላይ በክትትል ተያዘ።"

መሰለች ከጠለፋ አምልጣ ስትመለስ ጉዳዩን በሕግ ሳይሆን በሽምግልና ለመፍታት መሞከሩን ኪያ ትነቅፋለች።

"የካሳ ገንዘቡን መልሺ ካለበለዚያ ሚስቴ ነሽ ነው እያለ የነበረው። ጠለፋ በራሱ ወንጀል ነው። [ካሳውን] ለሠራው ሥራ እንጂ ሚስቱ እንድትሆን እንደ ጥሎሽ አይደለም የሰጣት።"

ማኅበረሰቡ ዘንድ በተፈጠረው 'ካሳ ከፍሎባታል' የሚል የተዛባ ምልከታ ምክንያትም ሊያስጥላት የሞከረ እንደሌለ ትናገራለች።

መሰለች "ከግለሰቡ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበራት" የሚል የተሳሳተ ትርክትም እንደተፈጠረም ታክላለች።

ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም. በሰሜን ቤንች ወረዳ ኮምዩንኬሽን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ የወጣ መግለጫ "ፍቅረኛውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ" የሚል ነው።

የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ተደርጎ መቅረቡ የተፈጠረውን የተዛባ ምልከታ እንዳጠናከረው ኪያ እና ዮርዳኖስ ያስረዳሉ።

"ተጠልፋ ተወሰደች እንጂ፣ ከጠለፋዋ አምልጣ መጥታ ካሳ ተከፈላት እንጂ የፍቅር ግንኙነት አልነበራቸውም" ትላለች ኪያ።

ዮርዳኖስም "በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የቀረበው ፍቅረኛዋ የሚል ነው። ድርብ ጋብቻውን የመቀበል ነገር ነው። የተሳሳተ ትርክት፣ ጉዳዩ በዚያው ተዳፍኖ እንዲቀር እና ትክክለኛ ፍትሕ እንዳይሰፍን ያደርጋል" በማለት ታስረዳለች።

"ፍቅረኛዋ ገደላት" የሚለው ትርክት በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥም ጫና እንደሚያሳድር እና እውነታውን እንደሚያዳፍን ታክላለች።

ጠለፋን ጨምሮ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በባህላዊ መንገድ በሽምግልና "ለመፍታት" መሞከር ችግሩን የበለጠ እንደሚያባብሰው የመብት ተሟጋቾቹ ያሰምሩበታል።

"ከፈቃድ (consent) ጋር በተያያዘ 'ካሳ ስለከፈለባት ሚስቱ መሆን ትችላለች' የሚለው በራሱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ያሳያል" ትላለች ኪያ።

ሴቶች አንድን የወንጀል ጉዳይ ለፖሊስ ካሳወቁ በኋላ ተጠርጣሪዎች የበቀል እርምጃ እንዳይወስዱባቸው ደኅንነታቸው መጠበቅ እንዳለበትም ታስረዳለች።

ለሴቶች በቂ ከለላ ከመንፈግ በተጨማሪ ጥቃት ሲደርስባቸው እነሱኑ መልሶ መውቀስ (victim blaming) ሌላው ችግር ነው።

"'ከፍሎባታል' የሚለው ሴቶችን መውቀስ ነው። ሴቶችን ለፆታዊ ጥቃት የሚያጋልጡ ልማዶችን እና ጥቃትን በዝምታ ማለፍን መከላከል አለብን" ስትል ኪያ ታስረዳለች።

አቶ ኤፍሬም በተጠርጣሪው ላይ "የከባድ ግድያ ክስ" መመሥረቱን ይናገራሉ።

መጀመሪያ ላይ "የጠለፋ ሙከራ" ሲያደርግ፣ በወረዳ ፍርድ ቤት ክስ ቢቀርብበትም በአገር ሽማግሌ ጫና፣ መሰለች ለፖሊስ የሰጠችውን ቃል እንድትቀይር መደረጓን ይተቻሉ።

"እኛ ጋር እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በተደጋጋሚ ያጋጥማሉ። ካሳ እንድትቀበል አድርገው ፍርድ ቤት ሄዳ ቃል እንድትቀይር ተደርጋለች። እሷም በተጽዕኖ 'ሊጠልፈኝ አይደለም፤ ቤተሰበቼን ከርቀት አይቼ ነው ደንግጬ የጮህኩት' ብላ በዚያ ምክንያት ታስራ ምርመራ ተደርጓል።"

ግለሰቡ ለመሰለች የከፈለው ካሳ "ለክስ ያወጣችው ወጪ" እንደሆነ ይናገራሉ።

ከጠለፋ ሙከራ ክስ ነጻ ከወጣ በኋላም "ገንዘቤን አስጨርሳኛለች" በሚል ቂም ይዞ ቆይቷል። መሰለች ግን ጉዳዩ ያለቀ መስሏት ሰላማዊ ኑሮዋን ቀጥላ ነበር።

በሽማግሌ ጫና ለፖሊስ የሰጠችውን ቃል እንድትቀይር ተጽዕኖ መደረጉም "መጨረሻ ላይ መስዋዕት አስከፍሏል" ሲሉ አቶ ኤፍሬም ይናገራሉ።

"በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ብዙ ደላሎች አሉ። ማስረጃ ለማጥፋት የሚኬድበት ጥግ ነው። በዚያም በዚህ ብለው በተደራጀ መንገድ ቃሏን እንድትቀይር፣ ወጪዋን [በካሳ መልክ] እንድታገኝ አድርገዋል" ይላሉ።

የፍትሕ ሒደቱን "በማሳሳት" ተጠርጣሪው በወቅቱ የነበረው ጠበቃ እንዲሁም መሰለች ላይ ጫና ሲያደርጉ የነበሩ የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።

ግለሰቦቹ በዋስ የወጡ ሲሆን፤ ከመካከላቸው አራቱ ላይ ፖሊስ ማጣሪያ እንዳደረገ እና ክስ እንደሚመሠረት ተናግረዋል።

አክሽን ኤድ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች እና ከአርቲክል 35 በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ "ለሌሎች መብት ስትታገል እና ፍትሕ ስትጠይቅ የኖረችው ወጣት መሰለች ካሽንቴት ገና በለጋነቷ የምረቃት ካባዋን ሳትለብስ እና የለፋችበትን ውጤት ሳታይ ሕይወቷ ማለፉ ያስቆጫል" ብለዋል።

"በተለይም ለሰብአዊ መብቱ ስትሟገትለት እና ስታገለግለው በነበረው ማኅበረሰብ መሀል ጩኸቷ ሰሚ አጥቶ ለሞት ተላልፋ መሰጠቷ ሐዘናችንን መሪር አድርጎታል" በማለትም ገልጸዋል።

ጠለፋ ወንጀል ሆኖ ሳለ በካሳ ጉዳዩ ተድበስብሶ መቅረቱን ተከትሎ ግለሰቡ "ካሳ ስላስከፈልሽኝ ሚስቴ ሁኚ፤ አለበለዚያ የካሳውን ገንዘብ መልሺ" እያለ ተከታታይ ዛቻ ሲያደርስባት መቆየቱ ተመልክቷል።

መሰለችም "እኔ እንኳን ለራሴ መብት ለሌሎችም የምሟገት ነኝ፤ ሁለተኛ ሚስት አልሆንም" የሚል ምላሽ ሰጥታለች።

አቶ ኤፍሬም እንደሚሉትም፤ ተጠርጣሪው "ሲከታተላት" እንደነበረ ተገልጿል።

"እሷ ስንት መስዋዕትነት ከፍላ፣ ታስራ፣ ነጻ የወጣው ሰውዬ ይከታተለኛል ብላ ያሰበች አልመሰለኝም። እሱ ቂም ይዞ እስከ መጨረሻው እተከታተላት ነበር" ብለዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ፤ የሕግ ሥርዓቱ በአግባቡ ባለመፈጸሙ፣ በሽምግልና ጣልቃ ገብነት ፣ በማኅበረሰቡ ዝምታ እና በጎጂ ባህል ምክንያት የመሰለች ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ መቀጠፉን ተናግረዋል።

"መሰለች የራስዋንም ሆነ የሌሎችን ሴቶች መብት ለማስከበር ለነበራት ቁርጠኝነት ክብር እየሰጠን በስሟ ፍትሕ እንጠይቃለን" ሲሉም አሳስበዋል።