ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢዜማ በአርሲው ጥቃት ባለሥልጣናት ራሳቸውን "ከተጠያቂነት ነፃ" ማድረጋቸውን ሲኮንን፣ አብን ክስተቱን "የመንግሥት አካላት ውድቀት ማሳያ ነው" አለ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በኦሮሚያ ክልል አርሲ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘው፣ ክስተቱን በተመለከተ የክልሉ መንግሥት የሰጠውን ምላሽ ኮነኑ።
ፓርቲዎቹ ይህን የገለጹት ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ ነው።
በአሮሚያ ክልል በአዲሱ መዋቅር በደቡብ ምሥራቅ ዞን ውስጥ በተካተተው አርሲ ዞን በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በሽርካ ወረዳ ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከዚህኛው ጥቃት ቀደም ብሎ ጥቅምት 10 ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ አጎራባች በሆነው መርቲ ወረዳ ጎራ ሲሊንጎ ቀበሌ ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞ ከ15 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ይህንን ጥቃት አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል እሁድ ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቷል። የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ ጥቃቱን ያደረሰው "በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ" ነው በማለት ከሠዋል።
ኃላፊው አክለውም "መንግሥትበሰሜን ኢትዮጵያ በወሰደው የአገርን አንድነት፣ ሉዓላዊነት የማስጠበቅ እርምጃ መቋቋም ያቃታቸው የጽምዶ አባላት ይሄኛውን አቅጣጫ ለማሳት የፈጽሙት" መሆኑን ተናግረዋል። ኢዜማ በበኩሉ በኦሮሚያ ክልል በኩል የተሰጠው መግለጫ "ኢ-ሞራላዊ ተግባር ማስያ" በማድረግ ገልጾታል።
"የመንግሥት ባለሥልጣናት ችግሮቹ ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ እንዳልነበረ በሚመስል መልኩ ወቅታዊ ጉዳዮችን ተጠቅሞ እራስን ከተጠያቂነት ነፃ ማድረግ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ኢ-ሞራላዊ ተግባር ነው" ሲል ኢዜማ በመግለጫው ወቅሷል።
ኢዜማ አክሎም "ከሰሞኑ በአርሲ ለተፈፀመው ጥቃት በኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የተሠጠው መግለጫም ለዚህ ጥሩ ማሣያ ነው" ብሏል።
ፓርቲው ይህንን መሠል ችግሮች የመከሰታቸውን ምክንያቶች ምን እንደሆኑ አጥንቶ መፍትሔ የሚላቸውን ሐሣቦች ባለፉት ዓመታት ሲጠቁም መቆየቱን" በማስታወስ፣ መንግሥት የዜጎችን ሕይወት "መታደግ አለመቻሉ" እና "የዜጎች ነፍስ መቀጠፉ መራር ቁጭት እንደሚፈጥርበት" ገልጿል።
ኢዜማ የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ የሚገኙ የደኅንነት ችግሮች "ታጣቂ ኃይሎች ብቻቸውን የሚፈጽሙት ሳይሆን በመንግሥት ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችም ጭምር የሚሳተፉበት መሆኑን" አስታውቋል።
በተመሳሳይ መልኩ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ በአርሲ ሽርካ ወረዳ "ያልተቋረጠ ጥቃት" እንደሚፈጸም ገልጿል።
እነዚህ ጥቃቶች "በንጹኃን ዜጎች እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናት እና ምእመናን ላይ የሚፈጸመው" መሆናቸውን የገለጸው አብን ጥቃቶቹ "መንግሥትን መዋቅራዊ ድክመት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት እንዲሁም የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥታት የተጣለባቸው የታሪካዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት ውድቀት ማሳያ" ናቸው ብሏል።
"የዜጎች ሕይወት በየቦታው እንደ ቅጠል ሲረግፍ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን እና ወንጀለኞችን የሚያስቆም ቁርጠኝነትና አስተማማኝ አሠራር አለመዘርጋቱ የመንግሥታቱን ቸልተኝነት እና የፍትህ መጓደል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ" ነው በማለት ወቅሷል።
አብን በዚህ መግለጫው "የ[ኦሮሚያ]ክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ከተለመዱት የኩነኔ እና ሰበብ ፈላጊ መግለጫዎች በመውጣት፣ የዜጎችን ሕይወት እንዲታደጉ" ጠይቋል።
በተጨማሪ "ሕዝብን የሚያረጋጋ እና አስተማማኝ የደኅንነት መዋቅር በአፋጣኝ እንዲዘረጉ" አሳስቧል።
ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመግለጫቸው መንግሥት "በጥቃቱ ላይ ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ እጅ ያላቸውን አካላት፣ ሥልጣናቸውን አለአግባብ ተጠቅመው ዜጎችን ለጥቃት ያጋለጡት የመንግሥት ኃላፊዎችን" ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከ60 በላይ የቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን መገደላቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት ጥቃቱን በማስቆም፣ ፈጻሚዎቹን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንዲሁም ለነዋሪው ጥበቃ እንዲያደርግ ተማጽኗል።
በአርሲ ውስጥ ለበርካቶች ሞት እና ጉዳት ምክንያት የሆነውን ጥቃት በተመለከተ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።