በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የእርሻ ምርት ላይ ስጋት የፈጠረው ክስተት

የፎቶው ባለመብት, Senait Gebru
አርሶ አደሯ ወ/ሮ ጠዓሞ ሐድሽ ላሞቻቸው እና በሬዎቻቸው ከመኖ እጦት የተነሳ መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ለቤተሰባቸው ቀለብ ምንጭነት የታረሰው የእርሻ መሬታቸው ዘንድሮ ፍሬ ባለመያዙ ተስፋ ቆርጠዋል።
በደቡብ ትግራይ ዞን በራያ አዘቦ ቀበሌ ሐወልቲ ነዋሪ የሆኑት ጠዓሞ "ዓመቱን ሙሉ ዝናብ አላየንም፤ እንስሶቻችን የሚበሉት አጥተው እየሞቱ ነው" ይላሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ማዕከላዊ፣ ሰሜናዊ፣ ሰሜን ምሥራቅ እና ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች በኤል ኒኖ ክስተት ምክንያት የክረምት ዝናብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ገልጿል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል በግጭት ምክንያት የእርሻ ወቅቶች በመደናቀፋቸው ምክንያት 21 ወረዳዎች ከፍተኛ የረሃብ ስጋት ውስጥ ሲሆኑ 2.45 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ነሐሴ መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በአፋር ክልል ያቄር በተባለ ስፍራ ከ18,000 በላይ ከብቶች በውሃ እና በመኖ እጥረት ምክንያት ሞተዋል።
በትግራይ ክልል ሦስት ወረዳዎች ውስጥ ያሉ ገበሬዎች በከባድ የዝናብ እጥረት ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው እርሶ አደሮች እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ይናገራሉ።
በተከሰተው የአየር ሁኔታ ለውጥ በደቡባዊ፣ በደቡብ ምሥራቅ እና በመካከለኛው ዞኖች (በከፊል) ድርቅ እና በአንዳንድ ዝናብ በጣለባቸው ወረዳዎች ደግሞ ከባድ የበረዶ ዝናብ እና ጎርፍ ተከስቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ተመራማሪዎች ከጥር ወር ወዲህ ኤል ኒኖ የተባለው የአየር ሁኔታ ክስተት ተጨባጭ አደጋ መደቀኑን ሲናገሩ ቆይተዋል።
በርካታ የአየር ሁኔታ ተከታታይ ተቋማት እንደሚሉት ይህ ክስተት እስከ አሁን ከተመዘገቡት የከፋ ሆኖ ሊዘልቅ ይችላል በማለት ከዚህ በፊት ከነበሩት የበለጠ እና ያልታየ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ይህም በዓለም አቀፍ የሜትሮሎጂ ድርጅት መሠረት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኞቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የከፋ የአየር ሁኔታ እንዲከሰት ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲም በግንቦት ወር የክረምት ትንበያው ላይ የደቡብ እና የምሥራቅ ትግራይ አካባቢዎች፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ የአፋር እና የምሥራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች ከመደበኛው በታች ዝናብ እንደሚገያኙ እና በነሐሴ ወር፣ የሰሜን እና የምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች ደረቅ እንደሚሆኑ ገልጾ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Alem/supplied
"ምንም ተስፋ የለንም"
"እንዲህ ዓይነት ድርቅ አይተን አናውቅም፤ ዝናብ የለም። በጣም አስቸጋሪ በሆነ ዓመት ውስጥ ነን" ሲሉ በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን የአሊቴና ጣቢያ አርሶ አደር የሆኑት ዓለም ምስግና ይናገራሉ።
ወረዳው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ መልክዓ ምድራዊ ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በክረምት ዝናብ እጥረት ምክንያት እንስሳት በምግብ እና በውሃ እጥረት እየሞቱ መሆኑን ተናግረዋል።
"…ይህ ወቅት ብዙ ምርት የምናገበኝት መሆን ነበረበት። ነገር ግን ከባድ ድርቅ አለ። ምንም ተስፋ የለንም፤ ፈጣሪ ያውቃል..." በማለት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
አብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ በድህነት እና በምግብ ዋስትና እጦት ውስጥ ስላለ የሴፍትኔት እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ተጠቃሚዎች እንደነበረም ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የራያ አዘቦ ወረዳ የኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ዓለም አሰፋ 112,000 እንስሳት ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን እና ወደ 67,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአገሪቱ አብዛኞቹ ክፍሎች መደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ ዝናብ ይጠበቃል።
የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም የምግብ እና እርሻ ድርጅትን ጨምሮ ስምንት ዓለም አቀፍ ተቋማት ኤል ኒኖ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ይህም ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን እና ጂቡቲን ጨምሮ በቀጣናው ያሉ አገራት ከመደበኛ ያነሰ ዝናብ እደንሚያገኙ የሚመያለክት ነው።
በዓለም ዙሪያ ኤል ኒኖ በቀጣይ ዓመት ተጨማሪ 49 ሚሊዮን ሰዎችን ለከባድ ረሃብ ሊያጋልጥ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት አስጠንቅቆ፣ በ45 ተጋላጭ አገራት ውስጥ እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎችን ቁጥር በ22 በመቶ ጨምሮ 274 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተንብይዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ነሐሴ ላይ ባወጣው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭት ምክንያት የምግብ ዋስትና ችግሮች እንዳጋጠማት፣ በተለይም የግብርናው ዘርፍ ትልቅ ፈተና እንደተጋረጠበት አመልክቷል።
ጨምሮም በአገሪቱ ማዕከላዊ፣ ሰሜናዊ፣ ሰሜን ምሥራቅ እና በምሥራቃዋ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ እጥረት ስላለባቸው ችግሩ እንደሚብስ አስጠንቅቋል። በተቃራኒው በኢትዮጵያ ደቡባዊ እና ደቡብ ምሥራቃዊ ክፍሎች ላይ ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ይጠበቃል።
ተጨማሪ ችግር
በትግራይ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል አዲስ ግጭት ይነሳል የሚል ስጋት በጨመረበት በዚህ ወቅት በዝናብ እና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ለሚኖሩ ገበሬዎች ተጨማሪ ስጋት ተፈጥሯል።
አርሶ አደሯ ጠዓሞ እንደሚሉት ቀደም ሲል ተመሳሳይ ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት ገበሬዎች ከብቶቻቸውን ይዘው ዝናብ ወደሚያገኙ አካባቢዎች መውሰድ የተለመደ ቢሆንም፣ "አሁን ግን ሰላማዊ ሁኔታ ስለሌለ ሁሉንም ቤት ውስጥ ነው የሚውለው" ሲሉ ይናገራሉ።
ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት በኋላ ብዙም መልሶ ያልተረጋጋው የትግራይ ክልል ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን እና ችግሩም ለቀጣይ ዓመታት ሊዘልቅ እንደሚችል የክልሉ የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለምበርሃን ሃሪፌዮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የፖለቲካ እና የደኅንነት ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የችግሩ ክብደት በዋናነት ከሚቀጥለው ጥር 2019 እስከ ጥር 2020 የሚታይ ይሆናል" ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመውን የክልሉን አስተዳደር የህወሓት መሪዎች ከተቆጣጠሩ በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት የተበላሸ ሲሆን፣ ለክልሉ የሚሰጠው አቅርቦት እና በጀት በመቋረጡ ችግር መከሰቱን ባለሥልጣናት ይገልጻሉ።
"ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች እርዳታ እያገኙ አይደለም። ከጦርነቱ በኋላ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ባለመካሄዳቸው የግብርናው ዘርፍ እንደተጎዳ ነው። ይህም በከፋ መልኩ ለድርቅ ተጋላጭ እያደረገን ያለው" ይላሉ አቶ ዓለምብርሃን።
ከዚህ ባሻገር ጦርነቱን ተከትሎ ክልሉ አብዛኛውን የግብርና ምርት ያገኝበት የነበረው የምዕራብ ትግራይ ዞን ከቁጥጥሩ ውጪ በሆነበት ወቅት "ከ600,000 ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በእጃችን የለንም" በማለት ብለዋል።
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት ምዕራብ ትግራይ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ኃይሎች እና አስተዳደር ስር ይገኛል።

የፎቶው ባለመብት, Alem/supplied
ኤል ኒኖ ምንድን ነው?
ኤል ኒኖ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመታት ባለ ልዩነት የሚከሰት ከባድ የአየር ሁኔታ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል።
በፓስፊክ ውቅያኖስ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚነፍሰው እርጥበት አዘል ነፋስ ሲዳከም የሚመለስበትም ሁኔታዎች ታይተዋል። ይህም ሞቃታማ አየር በምሥራቅ በኩል እንዲዛመት አድርጓል።
ከውቅያኖሶች ወጥቶ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው ሙቀት የዓለም የሙቀት መጠንን የሚጨምር ሲሆን፣ የዝናብ ወቅትንም ያዛባል።
ተመራማሪዎች ኤል ኒኖ እንደተከሰተ የሚያውጁት ከባሕር ጠለል በላይ የሙቀት መጠን በአማካይ ከ0.5 ዲግሪ ሴልሽየስ ወይም ከዚያ በላይ ሲሆን ነው። ይህም የነፋስን አቅጣጫ የማስቀየር፣ እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታን የመለወጥ አቅም አለው።
አሁን ላይ ያለው ግን ከ2 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ ተለክቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም ሚቲዮሮሎጂ ቢሮ እንዳለው በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የሙቀት መጠኑ 3 ዲግሪ ሴልሽየስ ሊደርስ ይችላል። ይህም ከአውሮፓውያኑ 1950 ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ምን አልባትም ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በጣም ከፍተኛው ክስተት ይሆናል።
ሌሎች የአየር ንብረት ተመራማሪ ቡድኖችም የዩኬው ሚቲዮሮሎጂ ቢሮ ከመዘገበው የበለጠ 4 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚሆን ተንብየዋል።
ይህ ከሆነ ምንም እንኳን አስቀድሞ ይህን መናገር ባይቻልም "በ500 ወይም 1000 ዓመታት ውስጥ እጅግ አስከፊው የኤል ኒኖ ክስተት ሊሆን ይችላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚከሰት የሚጠበቀው የኤል ኒኖ የአየር ሁኔታ ክስተት በምሥራቅ አፍሪካ ድርቅን እና ጎርፍን ጨምሮ ከባድ የአየር ሁኔታን ሊያስከትል እንደሚችል ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
የዴንማርክ የስደተኞች መርጃ ተቋም ነሐሴ አጋማሽ ላይ ባወጣው ሪፖርት፣ እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በኡጋንዳ በጎርፍ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
በአውሮፓውያኑ 2023 በቀጣናው ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ተፈናቅለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ እነዚህን ክስተቶች የበለጠ ከባድ ወይም ተደጋጋሚ እያደረገው መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አሁንም የለም፤ ነገር ግን የዓለም ሙቀት መጨመር እነዚህ ክስተቶች እንዲጨምሩ ሊያደርግ ይችላል።















