ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአርሲ ጥቃት ጋር ተያይዞ 'ቁስለኛ ያነሱ እና ቀብር ያስፈፀሙ' በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም. ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ የድረሱልኝ ጥሪ ሰምተው ወደ ስፍራው የሄዱ ከ20 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን አምስት ነዋሪዎች እና ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአዲሱ አደረጃጀት የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ውስጥ በሚገኘው የአርሲ ሽርካ ወረዳ ዋና ከተማ ጎቤሳ ጥቃቱ ከተፈፀመበት ቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ሕፃናትን የያዙ ሴቶችን ጨምሮ "27 ነዋሪዎች" በአካባቢው በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን እና በርካቶችም እየተፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የቢቢሲ የቤተ ክርስቲያን ምንጮች ጥቃቱን ተከትሎ ሴቶችን ጨምሮ "24 ሰዎች ገደማ" ታስረው እንደነበር ጠቁመው፤ አንዳንዶች ከቀናት እስር በኋላ ሲለቀቁ እስካሁን 13 ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከወረዳው እና ከዞን አስተዳደር ስለ እስሩ ምክንያት አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ምላሽ አላገኘም።
እየተካሄደው ያለውን ነዋሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃን በተመለከተ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች እንታሰራለን የሚል ስጋት በዘጋባው ውስጥ ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል።
እስሩ እየተፈጸመ ያለው ከጥቃቱ በተረፉት፣ የተጎዱትን እና የሞቱትን ለማንሳት በደረሱት እና ለቅሶ ለመድረስ በመጡ ሰዎች ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግዋል።
"የተገደሉ እናት አባቱን ሊቀብር፤ አስከሬን አንሱልን፤ ድረሱልን ያልናቸው ወንድሞቻችን ናቸው [የታሰሩት]። አባቷን ልትቀብር፤ እናቷን ልትቀብር፤ ወንድሟን ልትቀብር የመጣች ሴት፤ እነዚህ ናቸው የታሰሩት" ሲሉ አንድ ነዋሪ ስለታሳሪዎቹ ማንነት ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ከጥቃቱ በኋላ "ከ14 [ቅዳሜ] ማታ ከተመለሱ ጀምሮ ቤታቸው ከበባ ተደርጎ፤ ሌሊት የተገኘውም ታስሮ ነው ያደረው። በ15 እሑድ ዕለት እንዳለ አፍሰው ነው ያስገቧቸው" ብለዋል ነዋሪው።
ሌላ ነዋሪ ደግሞ ስለታሳሪዎች ማንነት ሲገልፁ "በዚያ ዕለት [ጥቃቱ በተፈፀመበት ቀን] የጮሌን ምድር የረገጠ ወይም ለመርዳት የተባበረ፤ ሊቀብር የመጣውን ሁሉ እያፈሱ አስረዋል" ብለዋል።
በጥቃቱ የቆሰሉ ሌላ ነዋሪም ይህኑ የሚያጠናክር ሀሳብ አጋርተው፤ "ስለአተረፉን የሚፈለጉ ሰዎችም አሉ" ብለዋል።
ከታሳሪዎቹ ውስጥ ቤተሰቧ የተገደለባት እና ከሁለት ልጆቿ ጋር የታስራ የነበረች የቤተሰባቸው አባል ከአንድ ቀን እስር በኋላ መለቀቋንም አመልክተዋል።
በጥቃቱ እህታቸውን ጨምሮ አምስት ቤተሰባቸው እንደተገደሉባቸው የተናገሩ ሌላ ነዋሪ በፀጥታ ኃይሎች እየተፈለጉ በመሆኑ ሐዘን መቀመጥ እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"እየተፈለክ ነው ሲሉኝ አሁን ተደብቄ ነው ያለሁት፤ እንግዳ [ለቅሶ የሚደርስ ሰው] እንኳ ለመቀበል ተቸግሪያለሁ። በአካባቢያችን፣ በባህላችን ሸንጎ አለን፤ ይህን ሸንጎ ለመቀበል አስቸገሩኝ" ሲሉ ሐዘናቸውን በባህላቸው መሠረት መወጣት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
አንድ የቤተ ክርስቲያን ምንጭ ነዋሪዎቹ የታሰሩት "ለታጣቂዎቹ መረጃ ሰጥታችኋል" በሚል እንደሆነ ጠቁመው፤ ክሱን "የማይመስል" ብለውታል።
"ሐሰት ነው በምንም የሚገናኙ አይደሉም" ሲሉ ታሳሪዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ሌሎች ነዋሪዎችም በተመሳሳይ "'የተገደለው ሕዝብ ፋኖ ነው፤ እናንተ ደግሞ የፋኖ ደጋፊ፤ አደራጅ ናችሁ'" በሚል ለእስር እንደተዳረጉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁሉም ነዋሪዎች እና የቤተ ክርስቲያን ምንጮች በዚህ አይስማሙም።
ነዋሪዎቹ በሥራ እና ኑሮ ምክንያት ከተማ የገቡ የአካባቢው ተወላጆች እና ቤተሰቦቻቸውን ለመቅበር የመጡ "ንፁህ ሰው" መሆናቸውን ገልፀዋል።
"ሰላማዊ ሰዎች ናቸው፤ ግማሹ ግብርና ሥራ ሰርቶ ሱቅ ለመክፈት ወደ ከተማ የሄደ ነው" በማለት አንድ ነዋሪ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ታሳሪዎቹ እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የጥቅምት 14ቱ ጥቃት ክፉኛ ጉዳት በደረሰበት ጮሌ ቀበሌ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ከጥቃቱ በተጨማሪ በጎቤሳ ነዋሪዎች እስር መረበሻቸውን ተናግረዋል።
"እንዲሁ ቆመን እንሄዳለን እንጂ" ሲሉ የአካባቢው ማኅበረሰቡ የደረሰበትን ከባድ ሐዘን ተናግረዋል።
"ሰው በጣም አዝኗል። በጣም ሐዘን እና ስቃይ ላይ ነው ያለው።"
"ነገ እኛ ምን መጨረሻ አለን? ሌላ ቦታ ያሉት ቤተሰቦቻችን መጥተው ቀብራችን ላይ እንኳ እንዳይገኙ፤ ባለንበት ቦታ አፈር የሚያለብሰን ሰው እንዳይደርስልን እየተደረግን ነው" ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ ደግሞ "መኖሬ ራሱ ያስጠላኛል። የሞቱት ይሻላሉ እያልን ነው። ለመናገር እንኳ እንባ እያነቀኝ አስቸግሮኛል" ሲሉ እንባ እየተናነቃቸው ስሜታቸውን መግለጽ አቅቷቸዋል።
ቢቢሲ በነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ በአካባቢው እየተካሄደ ያለውን እስር በተመለከተ የወረዳ እና የዞኑን ባለሥልጣናት አስተያየት ለማግኘት ስልክ በመደወል እና በአጭር መልዕክት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት የባለሥልጣናቱ ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
አርሲ ሽርካ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመው ጥቃት ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ 60 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መግለጻቸው ይታወቃል።