በእስራኤል አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊውን በግልፅ መለየት አልተቻለም

የፎቶው ባለመብት, EPA/Reuters
ትናንት ማክሰኞ በእስራኤል በተካሄደው ወሳኝ አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊው በግልፅ እንዳልተለየ የድምፅ ቆጠራ ውጤቶች አመለከቱ።
እስካሁን ይፋ በሆኑት የመጀመሪያ ደረጃ የድምፅ ቆጠራ ውጤቶች መሠረት፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለረጅም ጊዜ የቆዩት ቤንያሚን ኔታንያሁም ሆኑ ተፎካካሪያቸው የቀድሞው የጦር ኃይሎች አዛዥ ጋዲ አይዘንኮት በተናጥል የፓርላማውን አብላጫ ድምፅ ማግኘት በሚያስችላቸው በመንገድ ላይ አይደሉም።
ሁለት የእስራኤል ሚዲያ ተቋማት ግምት እንደሚያመለክተው፣ የአይዘንኮት ፓርቲ የሆነው 'ያሻር' እና ከፓርቲው ጋር "የለውጥ ጥምረት" የመሠረቱ ሦስት ሌሎች የአይሁድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 120 መቀመጫ ባለው የእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) ውስጥ 51 መቀመጫዎችን ያገኛሉ።
የኔታንያሁ 'ሊኩድ' ፓርቲ እና ተጣማሪዎቹ የቀኝ አክራሪ እና እጅግ ወግ አጥባቂ የአይሁድ አጋሮቹም እንዲሁ 51 መቀመጫዎችን እንደሚያገኙ ተገምቷል።
ሌላ ሦስተኛ የሚዲያ ተቋም በበኩሉ ኔታንያሁ በሦስት መቀመጫዎች እንደሚመሩ ግምቱን አስቀምጧል።
ከዚህ ቀደም ባልታየ መጠን 18 ወይም 19 መቀመጫዎችን እንደሚያሸንፉ የተገመቱት ሁለት የአረብ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ሚና በውጤቱ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በማክሰኞው ምርጫ ድምፅ ለመስጠት የወጣው ሕዝብ ቁጥር በአሥርት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን የማዕከላዊ ምርጫ ኮሚቴው ገልጿል።።
የምርጫው ይፋዊ ውጤቶች ከሌሊቱ ጀምሮ ታትመው መውጣት ይጀምራሉ። ከጠቅላላው ድምፅ 10 በመቶውን የሚሸፍኑት በአብዛኛው በወታደሮች የተሰጡ ወደ 600,000 የሚጠጉ ድምፆች እስከ ሐሙስ ድረስ ሙሉ በሙሉ አይቆጠሩም።
የመጨረሻው ውጤት ከታወቀ እና ከሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ፣ የእስራኤል ፕሬዚደንት መንግሥት ለማቋቋም ከፍተኛ ዕድል አለው ብለው የሚያምኑትን የፓርቲ መሪ ይጠራሉ። ይህ ሂደት ሳምንታትን ሊወስድ የሚችል ነው።
በዚህ ሂደት መንግሥት መመስረት ካልተቻለ ደግሞ ሌላ ምርጫ ማካሄድ ግድ ይላል።
የምርጫው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶች በካን፣ ቻናል 12 እና ቻናል 13 ሚዲያዎች ይፋ ከሆኑ በኋላ፣ በቴል አቪቭ በሚገኘው የአይዘንኮት ያሻር ፓርቲ ዋና መሥሪያ ቤት የተሰባሰቡ ደጋፊዎቹ "ቢቢ [ኔታንያሁ] ወደቤትህ ሂድ!" እያሉ በደስታ ሲጨፍሩ ነበር።
ሚዲያዎቹ በወቅቱ ይፋ ያደረጓቸው ግምቶች የአይዘንኮት ቡድን በክኔሴት ውስጥ ከ52 እስከ 53 መቀመጫዎችን በማግኘት የበላይ እንደሚሆን ሲያመለክቱ፣ የኔታንያሁ ጥምረት 50 መቀመጫዎች እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።
"ታሪክ ሠርተናል" ያሉት አይዘንኮት "የሕዝቡን ውሳኔ የተረጋጋ እና ለሁሉም እስራኤላውያን ወደ ሚጠቅም ጽዮናዊ መንግሥት እንዲተረጎም እናደርጋለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ፣ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የመሸነፍ ምልክት አልታየም። ግምቶች ሊኩድ ፓርቲ በፓርላማው ውስጥ ትልቁ ፓርቲ ሆኖ እንደሚቀጥል ያሳያሉ።
የፓርቲው ደጋፊዎች ተጨንቀው እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ጨዋታው እስኪያበቃ ድረስ አይቆምም፣ ነገር ግን እያላበኝ ነው" ሲል ኢትዚክ የተባለ ደጋፊ ተናግሯል።
የኔታንያሁ አጋር የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳር፣ በግራው ቡድን የተጀመረው ደስታ "ጊዜውን ያልጠበቀ" መሆኑን ተናግረዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ግቪር ደግሞ የቀኝ አክራሪ ፓርቲያቸውን ደጋፊዎች፣ የመጨረሻው ውጤት "ሙሉ በሙሉ የቀኝ ክንፍ መንግሥት" እንዲመሠረት የሚያስችል እንዲሆን እንዲጸልዩ ጠይቀዋል።
ረቡዕ ንጋት ላይ የሚዲያ የምርጫውን ውጤት የሚገምቱት ሦስቱ የሚዲያ ተቋማት በግምቶቻቸው ላይ ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ካን እና ቻናል 13 ሁለቱም ቡድኖች በ51 መቀመጫዎች እኩል ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ቻናል 12 በበኩሉ ለኔታንያሁ ቡድን 52 መቀመጫዎችን፣ ለአይዘንኮት ቡድን ደግሞ 49 መቀመጫዎችን ሰጥቷል።































