ደቡብ ኮሪያዊ ፖሊስ የሥራ ጫና እንዳይበዛበት የጠፉ ሰዎችን ጉዳይ ሳይመረምር መቅረቱን አመነ

በቁጥጥር ሥር የዋለው ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, News1

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ደቡብ ኮሪያዊ ፖሊስ የሥራ ጫና እንዳይበዛበት በሚል የጠፉ ሰዎችን ጉዳይ ሳይመረምር መዝገብ መዝጋቱን እንዳመነ ተገለጸ።

ቡ የተባለው ፖሊስ ከሳምንታት በፊት በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የበዓል መዳረሻ በሆነችው ጄጁ ደሴት ይሠራ የነበረው ፖሊስ ፋይሎችን ቀድሞ በመዝጋት እና ቤተሰተቦቻቸው ለጠፉባቸው ሰዎች በመዋሸት ተከስሷል።

በደሴቱ ላይ የጠፉ ሰዎች ጉዳይ እልባት ሳያገኝ መጓተቱ ያስነሳውን ሕዝባዊ ቅሬታ ተከትሎ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ብቻ አራት አስከሬኖች አግኝቷል።

የፖሊሱ ቅሌት ይፋ ከወጣ በኋላ ፕሬዝዳንት ሊ ጄይ ሙዩንግ የፖሊስ ኃይልን በድጋሚ ለማዋቀር ቃል ገብተዋል።

መንግሥት ለፖሊስ ተጨማሪ ኃይል ለመስጠት ዕቅድ እንዳለው አስታውቆም ነበር።

የጄጁ ግዛት ፖሊስ እንዳለው ቡ የተባለው ፖሊስ ቢያንስ ሁለት ከፍተኛ ጉዳዮችን ሳይጠናቀቁ መዝገብ ዘግቷል። የሕዝብ ንብረት የሆነ ኤሌክትሮኒክስ በማጭበርበር እና ይፋዊ ሥራ በማሰናከል ተከስሷል።

በሁለቱም መዝገቦች ላይ የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት እንደሞከረ በመግለጽ ምርመራዎችን አቋርጧል። ነገር ግን የጠፉት ሰዎች የት እንዳሉ ለማወቅም ሆነ ደኅና መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥረት አላደረገም።

ፖሊስ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ቡ ምርመራዎችን ሳያደርግ መቅረቱን አምኗል። "የጠፋው ግለሰብ አዋቂ ስለሆነ ብዙም ግድ አልሰጠኝም። መዝገቡ ካልተዘጋ ብዙ ሥራ ማከናወን ይጠበቅብኛል። መዝገቡን እንድዘጋ ጫና ስለሚበዛብኝም በሐሰት ዘግቼዋለሁ" ብሏል።

ከጠፉት ሰዎች አንዷ የ37 ዓመቷ ጃን ሚ-ራን ትባላለች። ግንቦት ላይ መጥፋቷን ለፖሊስ ያስታወቀው የወንድ ጓደኛዋ ነበር።

ቡ የጠፋችውን ሴት እንዳነጋገራት እና ከፖሊስም ሆነ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር መነጋገር እንደማትፈልግ እንዳሳወቀችው ገልጿል። ኋላ ላይ በተደረገው ምርመራ ግን ይህ ቡ የፈጠረው ውሸት መሆኑ ተደርሶበታል።

ቡ ውሸቱን የፖሊስ ኮምፒውተር ውስጥ መመዝገቡ ተገልጿል። ጃን በመኪና አደጋ መሞቷን ገልጾም መዝገቡን ዘግቷል።

የጃን አስከሬን ባለፈው ሳምንት በዘንባባ ዛፍ አቅራቢያ ተገኝቷል።

ያለፈው ሐምሌ ላይ በ60ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰው መጥፋቱ ለፖሊስ ጥቆማ ተሰጥቶ ነበር።

ቡ ከጠፋው ሰው ጋር እንዳወራ እና ከማንም ጋር መነጋገር እንደማይፈልግ እንደነገረው ገልጿል። ነገር ግን ይሄም ውሸት መሆኑ ተደርሶበታል።

ግለሰቡ በያዝነው ወር አስከሬኑ ተገኝቷል።

ቡ ሌሎች 25 የጠፉ ሰዎችን ጉዳዮች ሳይመረምር መዝገብ እንደዘጋ ፖሊስ ያምናል። ከእነዚህ መካከል በሕይወት የተገኙ ሰዎችም አሉበት።