ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት የሚገነቡ የማዕድናት ማጣሪያዎች አህጉሪቱን ከምዕራባውያን ጥገኛነት ነጻ ያወጣሉ?

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali
በአዲስ አበባ፣ ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በኬንያ የባሕር ዳርቻ ላሙ፣ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት አሊኮ ዳንጎቴ የሚያስገነቡት የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ በቅርቡ መሠረተ ድንጋይ ተጥሎለታል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት የተፈጥሮ ሃብታቸውን አገር ውስጥ ማቀነባበርን አማራጭ አድርገዋል። አገራቱ ጥሬ ማዕድናትን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ አገር በቀል ፋብሪካዎችን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ይሄ ለውጥ በመላው አህጉሪቱ ያለውን የአገር በቀል ኢንዱስትሪ እድገት የሚያጠናክር እንዲሁም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም ከውጭ አገራት የሚገቡ ሸቀጦችን በመቀነስ ለአፍሪካ ምርቶች ዕድል ይሰጣል።
ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጣበት የኢትዮጵያ ፋብሪካ ወርቅን በአገር ውስጥ ለማጣራት እና ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርትን ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ሚና ይኖረዋል።
ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባውን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም ከኢትዮጵያ እስከ ጂቡቲ የሚዘረጋው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧምቧ ከአገር በቀል ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ከ660 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚወጣበት የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧምቧ ከጂቡቲ የወደብ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ፣ ዳዋሌ ነዳጅ ለማዘዋወር ይውላል።
በ16 ሚሊዮን ዶላር በኬንያ የሚገነባው የነዳጅ ማጣሪያ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፉ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ እና የኬንያ ፋብሪካዎችን በአፍሪካ ላለው አካሄድ እንደ ማሳያ ይሆናሉ።
መንግሥታት እና ባለ ሃብቶች ማዕድናትን ከማውጣት ባሻገር በአገር ውስጥ ማጣራት ወይም ማቀነባበር ላይ እንዲሁም የኢንዱስትሪ እድገት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'አፍሪካ በራሷ ላይ መንተራስ አለባት'
ከተጠቀሱት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ስማቸው ከሚጠቀሱ መካከል ናይጄሪያዊው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ ቀዳሚው ናቸው።
"በሌሎች ላይ ተንተርሰን ታላቅ አፍሪካን መገንባት አንችልም። ማንም ከውጭ መጥቶ ለእኛ አፍሪካን ሊገነባልን አይችልም። ያንን ማድረግ የምችለው እኛ ብቻ ነን" ይላሉ።
ዳንጎቴ በሲሚንቶ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በማዳባሪያ እና ሎጅስቲክስ ዘርፎች በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ኢንቨስት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ በዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም በነዳጅ ማስተላለፊያ ቧምቧ ላይ ካላቸው ኢንቨስትመንት በተጨማሪ በኬንያ የነዳጅ ማጣሪያም ሃብታቸውን አፍስሰዋል።
የኬንያ፣ ላሙ ነዳጅ ማጣሪያ የቀጣናውን የኃይል አቅርቦት ዘርፍ እንደሚለውጠው ይጠበቃል።
አፍሪካውያን አገራት ጥሬ የተፈጥሮ ሃብታቸውን ወደ ውጭ ልከው ምርቶችን መልሶ ከመሸመት ይልቅ በአህጉሪቱ ውስጥ በማጣራት መጠቀም እንዳለባቸው ዳንጎቴ ይናገራሉ።
"አፍሪካ ነቅታ በራሷን ምጣኔ ሃብት ላይ የምትሠራበት ጊዜው አሁን ነው" ይላሉ።
የአህጉሪቱ ዋነኛ የምጣኔ ሃብት ፈተና ምክንያቱ የንግዱ ዘርፍ የሚገጥሙት መሰናክሎች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
"ለአፍሪካ የምጣኔ ሃብት እድገት ትልቁ መሰናክል በአፍሪካ አገራት መካከል የሰዎች፣ የአገልግሎት እና የሸቀጦች ዝውውር መገደብ ነው። የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ስምምነት ይሄንን ችግር ይቀርፋል ብዬ አምናለሁ" ሲሉም ያክላሉ።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የተፈጥሮ ሃብትን በአፍሪካ አገራት ውስጥ በማጣራት እሴት መጨመር በሒደት እየመጣ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Dr. Marit
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ኮሚሽን ኃላፊ እና የተፈጥሮ ማዕድናት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ማሪት ቅጣው እንደሚሉት፤ ለውጡ መታየት የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2009 'አፍሪካ ማይኒንግ ሚሽን' ፕሮጀክት ሲጀመር ነው።
አፍሪካ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖራትም አብዛኞቹ የአህጉሪቱ አገራት ይህንን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ውጭ አገራት በመላክ የሚያገኙት የምጣኔ ሃብት ጥቅም ውስን ነው።
በአፍሪካ ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን ይህንን ችግር መነሻ በማድረግም 'አፍሪካ ማይኒንግ ሚሽን' ተጀምሯል።
ዶ/ር ማሪት እንደሚሉት፤ ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘው ገቢ የኢንዱስትሪ እድገት ማምጣትም ሆነ የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል አልቻለም።
የኢነርጂ አቅርቦት አማካሪ ምዌንዳ ንያጋ እንደሚሉት የሕዝብ ቁጥርም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት።
በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ወጣቶች የሥራውን ዓለም ስለሚቀላቀሉ መንግሥታት የምጣኔ ሃብት ዕድልን የማስፋት እና የሥራ ዕድል የማመቻቸት ጫና ውስጥ ይወድቃሉ።
"ለብዙ ዓመታት ታዳጊ አገራት ጥሬ እቃን ኤክስፖርት አድርገው በዚሁ ግብዓት የተዘጋጁ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ያስገባሉ" ይላሉ ምዌንዳ።
ከውጭ አገር የሚገባን ምርት በአገር በቀል ምርት መተካት "እምብዛም የተለመደ እንዳልነበረ" ይናገራሉ።
አሁን ላይ እየታየ ያለው የፖሊሲ ለውጥ ግን አካሄዱን እንደሚቀይር ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከወርቅ ኤክስፖርት ወደ ማጣራት
የአፍሪካ አገራት በተፈጥሮ ሃብታቸው እሴት ለመጨመር በሚያደርጉት ጥረት በዋነኛነት የሚጠቀሰው ወርቅ ነው።
ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ሌሎችም አገራት አገር በቀል ወርቅ ማጣሪያ ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም ወርቅ ለማጣራት ወደ ውጭ አገራት ይላክ ነበር።
አሁን ላይ 14 የአፍሪካ አገራት ወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች አሏቸው።
የደቡብ አፍሪካው 'ራንድ ሪፋይነሪ' ከአህጉሪቱ ትልቁ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ ነው። በ1920ዎቹ ከተመቋቋመ አንስቶ በዓለም አንድ ሦስተኛውን ወርቅ አጣርቷል።
በቅርቡ የወርቅ ማጣሪያ ከገነቡ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች።
ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
ዶ/ር ማሪት እንደሚሉት ጥቅሙ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ በላይም ነው።
"ለወጣቶች እና ሴቶች ጉልህ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። አገር በቀል ክህሎትን ለማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ ይረዳል" ይላሉ።
ማዕድናትን ማጣራት ብቻ የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት እንደማያበለጽግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ስኬታማ መሆን የሚቻለው በተፈጥሮ ሃብት ዙሪያ የኢንዱስትሪ ሰንሰለት ሲገነባ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ዶ/ር ማሪት የኢትዮጵያን የፎስፌት ዘርፍ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያ ፎስፌትን በጥሬው ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ግብዓቱን በመጠቀም ማዳበሪያ ማምረት ብትችል፤ ከውጭ የሚገባውን ምርት በመቀነስ የተሻለ የምጣኔ ሃብት ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ይላሉ።
በሶማሌ ክልል ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካም ለዚህ ተጠቃሽ ነው።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ መርዕድ ቱሉ እንደሚናገሩት፤ የምግብ ደኅንነት፣ ኃይል ማመንጨት እና የኢንዱስትሪ እድገት ይተሳሰራሉ።
አፍሪካ የኢነርጂ አቅርቦቷን እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዋን ስታሳድግ፤ ግብዓቶችን በአገር በቀል ፋብሪካዎች ማጣራት እና ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ዋጋ ማግኘት እንደምትችል ያስረዳሉ።
ቀጣናዊ ትስስር ያለው ሚና
አገራት ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ከመገንባት ይልቅ ተባብረው ከሠሩ የኢንዱስትሪ እድገት እንደሚረጋገጥ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
ዶ/ር ማሪት ቀጣናዊ ገበያ ያለውን ጉልህ ድርሻ ያስረዳሉ።
"ኢትዮጵያ ወርቅ ማጣሪያ ካላት ለምን ታንዛኒያም ተመሳሳይ ፋብሪካ ትገነባለች?" ይላሉ።
ታንዛኒያ ወርቅ ለማጣራት ወደ ኢትዮጵያ መላክ እንደምትችል ጠቅሰውም "ገበያ ማስተሳሰር፣ መሠረተ ልማት መጋራት እና ኢንቨስተሮች መሳብ ላይ መሥራት አለብን" ሲሉ ያብራራሉ።
እንዲህ ላሉ ትብብሮች ማሳያ የሚሆነው 'ሎቢቶ ኮሪደር' ነው። አንጎላ፣ ዛምቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በባቡር ሐዲድ እና በወደብ ልማት የሚያስተሳስር የማዕድናት እንዲሁም ሌሎች ሸቀጦች መጓጓዣ ነው።
በምሥራቅ አፍሪካም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን በላፕሴት ፕሮጀክት ይተሳሰራሉ።
ላፕሴት ከቀጣናው ግዙፍ መሠረተ ልማቶች መካከል ይጠቀሳል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ለመጓጓዣ የሚወጣውን ገንዘብ እንደሚቀንሱ፣ የተሻለ ገበያ እንደሚፈጥሩ እና የምጣኔ ሃብት ትስስርን እንደሚያጠናክሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የአፍሪካ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ትኩረት ቢስብም ፈተናዎች እንደሚገጥሙትም ያስጠነቅቃሉ።
የመሠረተ ልማት ክፍተት፣ የፋይናንስ እና ኢነርጂ ውስንነት እንዲሁም የንግድ ፈተናዎች ይጠቀሳሉ።
እነዚህ መሰናክሎች በበርካታ አገራት ምርታማነት እና የኢንዱስትሪ እድገትን እንደሚፈታተኑ ያስረዳሉ።
የኢነርጂ አቅርቦት አማካሪ ምዌንዳ "ታሪካዊ ፈተናዎችም አሉ። የተለመደው አሠራር ጥሬ እቃን ኤክስፖርት አድርጎ በዚሁ ግብዓት ተሠርቶ ያለቀውን ምርት በውድ ዋጋ ገዝቶ ማስገባት ነው" ይላሉ።
ይሄንን ለመለወጥ ጊዜ እንደሚወስድም ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ቁጥሩ እየጨመረ ያለው ወጣት የአፍሪካ ሕዝብ ለኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
"ትልቁ ዕድላችን ሕዝባችን ነው። አምራች፣ በፍጥነት እያደጉ ያሉ ኢኮኖሚዎች እና ሰፊ ሸማች አለ። ይህም ትልቅ ዕድል ነው" ይላሉ ባለሙያው።
ለአሥርት ዓመታት ብዙ የአፍሪካ ምጣኔ ሃብቶች ጥሬ እቃን ወደ ውጭ በመላክ እና እሴት የታከለባቸው ምርቶችን መልሶ በመግዛት ላይ ተንተርሰው ቆይተዋል።
አሁን ላይ መንግሥታት፣ ኢንቨስተሮች እና ፖሊሲ አውጪዎች በዚህ አካሄድ ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።
ስኬታማነታቸው የሚወሰነው በኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት፣ በቀጣናዊ ትስስር እና ውጤታማ ትግበራ ይሆናል።































